ተሽከርካሪዎቹ የአገልግሎት መስጫ መለያ ቁጥር በመውሰድ ወደ ስራ እየገቡ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
የትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው ቁጥራቸው ከ10ሺ የሚልቁ የታክሲ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ ወስደው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
በቅርጫፍ ጽ/ቤቱ የህዝብና ጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት አደረጃጀት ስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ነጋ እንደሚናገሩት እኝህን ተሽከርካሪዎች በአግባቡ ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጡ በመቆጣጠር ረገድ የስምሪት ባለሙያውም ሆነ ተቆጣጣሪው ከትራፊክ ፖሊስ አባላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ ስራን እየሰራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የምሽት የታክሲ አገልግሎት ፍትሀዊ፤ተደራሽ እና በዘፈቀደ የሚንቀሳቀሱ ታክሲዎችን ለመቆጣጠር ብሎም ወንጀል መከላከልን መሰረት ባደረገና የተገልጋይ እርካታን ባገናዘበ መንገድ እንዲሰጥ 200 የሚሆኑ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎችን በመለየት ከትራፊክ ዳይሬክቶሬት ጋር በመቀናጀት አገልግሎት እንዲሰጡ ህጋዊ የመለያ ቁጥር በመስጠት ወደስራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ስራ ውስጥም በተለይ ፖሊስ ኮሚሽን ስራውን በሀላፊነት በመያዝና አፈፃፀሙን በመከታተል ውጤታማ እንዲሆን ከትራንስፖርት ባለስልጣን ጋርተቀናጅቶ እየሰራ ላለው ስራም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢኒስፔክተር ይሔነው ሽፈራው በበኩላቸው የቁጥጥር ስራን ይበልጥ አጋዥ የሆነውን የሌሊት ታክሲ መለያ ቁጥር በማዘጋጀት 200 ለሚደረርሱ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች መሰጠቱ ነዋሪው ለተለያዩ ጉዳዮች ሌሊት ላይ መንቀሳቀስ ቢያስፈልገው ያለስጋት እንዲንቀሳቀስ ከማስቻል ባለፈ በታክሲ አገልግሎት ሰበብ በወንጀል ላይ የሚሰማሩትን ለመቆጣጠር እገዛው ሰፊ ነው ብለዋል፡፡
እኝህ የሌሊት ታክሲ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎችም አንድም ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎትን ይሰጣሉ ጎን ለጎንም በፀጥታ ስራው ላይ የድርሻቸውን ያበረክታሉ ብለዋል፡፡
ሁሉም የታክሲ አገልግሎት መስጠት ስራ ላይ የተሰማራ አሽከርካሪ ሊረዳ ሚገባው ከተፈቀደለት አሽከርካሪ ውጭ በሌሊት የታክሲ ስራ ላይ መሰማራት ቅጣት እንደሚያስከትል ነው ብለዋል፡፡


