በድሬ ፔትሮሊየም ካምፓኒ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የነዳጅ ማደያ ስራ ጀመረ::

    የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ እና ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የተመረቀው ይህ የነዳጅ ማደያ በቀን 250 ሺህ ሊትር ነዳጅ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን ለ24 ሰዓታት ያለማቋረጥ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን የድሬ ፔትሮሊየም ካምፓኒ ተወካይ የሆኑት አቶ አለማየሁ ደነቀ ተናግረዋል፡፡ካምፓኒው ለምስራቅ ሀረርጌ ያለውን የነዳጅ ችግር በሚችለው አቅሙ ለመቅረፍ እንደሚሰራ ተወካዩ ገልጸዋል፡፡
    በተለይ አሁን ላይ የሚታየውን በህገ-ወጥ መንገድና በኮንትሮባንድ ነዳጅ የመሸጥ ሁኔታን በተመለከተ ተወካዩ ሲያብራሩ ካምፓኒው ከሚመለከተው ከመንግስት አካል ጋር በገባው ውል መሰረት ከነዚህ ህገ ወጥ መንገዶች በጸዳ ሁኔታ ስራውን እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡
    በቀጣይ ድሬ ፔትሮሊየም ካምፓኒ በመልካ መንገድ ላይ አዲስ ተጨማሪ የነዳጅ ማደያ ለመክፈት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው ከማደያው በተጨማሪ 500ሺህ ሊትር የመያዝ አቅም ያለው የነዳጅ ዲፖ በቀጣይ ስራ በሚጀምረው ማደያ እንደሚካተት አቶ አለማየሁ ጠቁመዋል፡፡