በአስተዳደራችን የኮሮና ስርጭት እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ በሳምንቱ የ8 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

    ከድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የኮቪድ – ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተዘጋጀ መግለጫ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ወረርሽኙን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ ቁጥር 30/2013 ዓ/ም በመላ ሀገሪቱ ከመጋቢት 20/2013 ዓ/ም ጀምሮ እንዲተገበርና በመመሪያው የተጠቀሱ የመከላከል ተግባራትን በሚተላለፍ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን የኮሮና ስርጭት እጅግ አሳሳቢ በሆነበት በአስተዳደራችንም ይኸው መመሪያ የሚተገበር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
    በተደጋጋሚ ስንገልፅ እንደቆየነው በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ አስገዳጅ የጥንቃቄ እርምጃዎች ለመፈፀም ፍቃደኛ ያለመሆንና በተለይም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ያለማድረግ፤አካላዊ ርቀትን ያለመጠበቅና የእጅ ንፅህናን አለመጠበቅ እንዲሁም በተቋማት ደረጃ ማስክ ላላደረገ ሰው አገልግሎት እንዳይሰጥ ቢወሰንም ይህ ባለመተግበሩ ምክንያት የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑን እና በሳምንቱ የ8 ሰዎች ህይወት አልፏል የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ዩሱፍ ሰዒድ ዛሬ የኮቪድ – ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ መጋቢት 23 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ፡፡
    ለአብነት ያህልም በአስተዳደራችን በዚህ ሳምንት ያለውን የስርጭትና የሞት መጠን ብናይ ናሙና ክተወሰደላቸው 654 ሰዎች 196 ያህሉ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን በሳምንቱ የ8 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በትናንትናው ዕለት ብቻ ከኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል በህክምና ላይ የነበሩ የ3 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት 20 ሰዎች ህክምና ላይ ይገኛሉ፡፡
    በመሆኑም በወረርሽኙ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ጉዳት ለመቀነስና ለመቆጣጠር የጥንቃቄ እርምጃዎችን መተግበር ብኛው መፍትሄ በመሆኑ ህብረተሰቡ እየተከሰተ ያለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በተሟላ መልኩ እንዲተገብር እያሳሰብን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሰዎች እንቅስቃሴና ማህበራዊ ተግባራት ላይ ክልከላ የሚጥለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ከመሆኑ ባሻገር ክልከላውን የሚጥሱ ደግሞ በወንጀል የሚጠየቁና እስከ ሶስት ዓመት በእስራት ሊቀጡ የሚችሉ መሆኑን ህጉ እንደሚያዝም መረዳት ያስፈልጋል፡፡
    በመመሪያው የተካተቱ ዋና ዋና ክልከላዎች፡-
    ●የኮሮና ቫይረስ ያለበት ግለሰብ ወደ ሀገር እንዳይገባ ተከልክሏል፡፡
    ●ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ወደ ማህበረሰቡ እንዳይቀላቀል አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንዲሁም ቫይረሱን ሊያስተላልፍ በሚያስችል ሁኔታ ንክኪ ማድረግ በሕግ ያስቀጣል፡፡
    ●በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፡፡
    ●ማንኛውም የንግድና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማስክ ያላደረጉ ደንበኞችንና ባለጉዳዮችን ማስተናገድ የለባቸውም፡፡
    ●ስብሰባን በሚመለከት ማንኛውም ሰብሳቢ አካል ተገቢውን የቅድመ መከላከል ተግባራት በመከወን የተሰብሳቢዎችን ቁጥር 50 ብቻ ማድረግ ይገባዋል፡፡
    የትራንስፖርት የስፖርትና ሌሎች ማህበራዊ መሰባሰቦችን በተመለከተ ተቋማቱ በሚያወጧቸው ዝርዝር ደንቦች የሚፈፀሙ ይሆናሉ፡፡
    ●የህጉን ዝርዝር ይዘትና አተገባበር በተመለከተ በሚመለከታቸው አካላት ማለትም በፌዴራል አቃቤ ህግ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ፤በድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የተጣሉ ክልከላዎችን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ የሚሰጡ ሲሆን ህጉን ለማስተግበር በአስተዳደር ደረጃ የተዋቀረው አስተግባሪ ግብረ-ሃይል የመመሪያውን ተግባራዊነት የሚከታተል ይሆናል፡፡