7ኛው የብስክሌተኞችና የእግረኞች ቀን መርሀግብር ድሬደዋ ላይ በተለያዩ መርሀ ግብሮች በድምቀት ተከብሯል፡፡

    አሽከርካሪዎችም ሆነ ተሳፋሪዎች ማስክን ባግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸው በመርሀግብሩ ተጠቁሟል፡፡
    ወር በገባ የመጨረሻው እሁድ ሚከበረው የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችና የእግረኞች ቀን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ድሬደዋ ላይ ተከብሯል፡፡
    በስነ_ስርዕቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰአዳ አዋሌ እንደተናገሩት መርሀግብሩ ማህበረሰቡ አማራጭ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችንና የእግር ጉዞ ባህልን እንዲያጎለብት ገንዛቤን በመፍጠር እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ታስቦ መርሀግብሩ በትራንስፖርት ሚኒስትር እና በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ትብብር ወር በገባ የመጨረሻው እሁድ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል፡፡
    በዚህም በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤን ለመፍጠር መቻሉንና ለውጦችም እየታዩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
    ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም አሁን ላይ ከምንግዜውም በላይ ስርጭቱ እየጨመረ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ ሌላ ስጋት ሌላ ፈተና ሀኗል ያሉ ሲሆን በተለይ ማህበረሰቡ ትራንስፖርትን ሲጠቀምም ሆነ አሽከርካሪው ሲያሽከረክር ማስክ የመጠቀም ባህሉ አናሳ ነው ብለዋል፡፡
    ይህን ለመከላከል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የመንገድ ላይ ቁጥጥርን በማጠናከር ማስክ በማያደርጉ ያለማክስ ተሳፋሪን ጭነው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ በወጣው ህግ መሰረት ጠበቅ ያለ የቅጣት እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል፡፡
    በእለቱ በመርሀግብሩ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ ባስተላለፉት መልእክት ሁሉም ማህበረሰብ ከምንግዜውም በላይ ራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና ወረርሽኝ ሊጠብቅ እንደሚገባ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በተለይ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ያሉ ባለድርሻዎች ለማህበረሰቡ ጤና ሲሉ ቁጥጥራቸውን እንዲያጠናክሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
    በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ጉልማ ታዬ እንዲሁም ከድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን ትራፊክ ዳይሬክቶሬት ተወካይ ኢኒስፔክተር ጌትነት ዳባ በመድረኩ ላይ ባስተላለፍት መልዕክት ማህበረሰቡ በትራፊክ አደጋ እንዳይጎዳ ህግን አክብሮ መንገዱን ባግባቡ እንዲጠቀምና የሞተር አልባ ተሽከርካሪንና የእግር ጉዞን ባህል እንዲያዳብር ተናግረዋል፡፡
    ከዚህም ጋር በማያያዝ እንደተናገሩት ከፊታችን ሳምንት ጀምሮም በተሽከርካሪዎች ላይ የማስክ ቁጥጥር እንደሚጀመር የገለፁ ሲሆን ከተፈቀደው ልክ በላይ ሚጭኑትም ላይ ጠበቅ ያለ ቅጣት እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡
    በእለቱ በተመረጡ ጎዳናዎች ላይ እንግዶችና በማህበረሰቡ የሳይክልና እግር ጉዞ በማካሄድ መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡