በድሬዳዋ አስተዳደር በ 350 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለሚገነባው የብረታ ብረትና ሲሚንቶ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የመሰረት ድንጋይ በዛሬው እለት ተቀመጠ ።

    በድሬዳዋ አስተዳደር ከመልካ ጀብዱ ወጣ ብሎ በኢንዱስትሪ ፓርክ አቅራቢያ በ 103 ሄክታር መሬት ላይ በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና በዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ኩባንያዎች በሽርክና ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ፣ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ እና ምክትላቸው አቶ ኢብራሂም ኡስማን፣ የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ፣ የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙአየሁ ታደለ የመሰረት ድንጋዩን አስቀምጠዋል።
    የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክሱ በሀገሪቱ በቂ የሲሚንቶና የብረታ-ብረት አቅርቦት እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር የማህበራዊና የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ትርጉም ባለው መንገድ ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር-ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል።
    የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ በበኩላቸው ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክሱ ድሬዳዋንና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ብልፅግና ለማሻገር አበርክቶው የጎላ መሆኑን ተናግረው ከተማችን ድሬደዋ የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ዋና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተሰነቀውን ራዕይ በአግባቡ ከዳር ለማድረስ ወሳኝ ይሆናልም ብለዋል።
    በድሬዳዋ የሚገነባው ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ አበርክቶው የጎላ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ተናግረዋል ።
    የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክሱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን ሚናው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።
    በተለይም ፋብሪካው በከተማው ላይ ሲገነባ ለከተማዋ ብሎም ለከተማው ነዋሪዎች በእጅጉ እንደሚጠቅምም የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ብዙአየሁ ታደለ ተናግረዋል ።
    በስነ-ስርዓቱ ላይ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ አባ-ገዳዎችና ኡጋዞች ተገኝተዋል።