የቴክኖሎጂ ፈጠራና ክህሎት ባለቤቶችን ማበረታታት ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ሊያበረክት የሚችለውን ሚና እንደሚያሳድገው ተገለጸ::

    በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ሁለተኛው የቴክኖሎጂ ፈጠራና ክህሎት ውድድር እንደአስተዳደር ተወዳድረው በተለያዩ ዘርፎች ድሬደዋን ለመወከል የተመረጡ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።
    በሽልማት ስነስረአቱ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቭስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በአለም ላይ ያደጉ አገራትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ አገራት የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ክህሎት የእድገታቸው ዋነኛ መሰረት እንደሆነ ተሞክሯቸው እንደሚያሳይ ገልፀው በአገራችን ለተጀመረው የለውጥ ጉዞና የብልጽግና መስመር ዘርፉ በሚገባው መጠን ዳብሮ ለእደገታችን ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጾ ለማላቅ የሚያስችሉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተቀርፀው ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
    በህዝቡ በተለይም በወጣቶች ዘንድ ከሃያስኩል ጀምሮ በየደረጃው የቴክኖሎጂ ፈጠራና ክህሎት ባለቤቶችን የፈጠራ ውጤቶችን ማበልጸግና ወደ ተግባር እንዲሸጋገር ማገዝ እናደሚገባ የገለፁት አቶ ከድር ወጣቶችና ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ታቅበው እራሳቸውንና ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ የምርምር እንዲሁም የፈጠራ ስራዎች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
    የድሬዳዋ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሳሊም ኡስማን በበኩላቸው ኤጀንሲው በአስተዳደራችን ውጤትን መሰረት ባደረገ ትምህርትና ስልጠና የኢንዱስትሪ ልማት የሚፈልገውን በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ ፤ ብቃቱን ያረጋገጠ ሙያተኛና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆነ ህብረተሰብ እንዲኖር ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ።
    በዘርፉ በየጊዜው የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ብሎም ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በየአመቱ የቴክኖሎጂ እና ክህሎት ውድድር እንደሚደረግ በ2013 ዓ.ም ለሁለተኛው አገር አቀፍ ውድድር ለመሳተፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ፤ የክህሎት ውድድር እና የካይዘን ውድድር አሰልጣኝ መምህራን ፤ ሰልጣኝ ተማሪዎች፤ጥቃቅን እና አነስተኛ መለስተኛ ኢንተር ፕራይዞች ተወዳድረው አሸናፊዎች ተለይተው ዥግጅቶች መጠናቀቃቸውን ኃላፊው አስረድተዋል ፡፡
    በቀጣይ ድሬደዋን ወክለው በአገር አቀፍ ደረጃ ለመሳተፍ የተመረጡ እጩ ተወዳዳሪዎችም በጥሩ ስነ ምግባር እራሳቸውን እና ከተማችውን የሚያስጠራ ስራ ይዘው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።