የትራንስፖርት መጨናነቁን ለመቅረፍ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

    ድሬዳዋ ከተቆረቆረች ከ115 ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡ በነዚህ ዓመታትም ከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች እድገትን አስመዝግባለች፡፡ ከነዚህ ዘርፎች ውስጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን በአግባቡ ሊያቀላጥፍ የሚችለው የመንገድ መስመር ዝርጋታ ስራ ዋነኛው ነው፡፡ እንደአስተዳደር ከዚህ አንጻር በርካታ ስራዎች የተሰሩና እየተሰሩ የሚገኙ ሲሆን በቀጣይም የከተማዋን ዕድገት ሊሸከምና የትራንስፖርት መጨናነቁን ሊያቃልል የሚችል ስራ በመሰራት ላይ ነው፡፡
    የፈረንሳይ መንግስት ባደረገው እገዛ በመጣ ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት ጥናት እየተካሄደ ሲሆን ጥናቱም ከከተማዋ እድገትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በትራንስፖርት እንቅስቃሴው ላይ ሊከሰት የሚችለውን መጨናነቅ ለመቅረፍ የሚያስችል ስለመሆኑ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ አህመድ መሐመድ ቡህ ገልጸዋል፡፡ አክውም የመንገዶች ሁኔታ፣ ልንጠቀም የምንችለውን የትራንስፖርት ማጓጓዣ ዓይነቶች ምን መምሰል እንዳለባቸውና የከተማው ነዋሪ ህበረተሰብም በምን ዓይነት መልኩ በትራንስፖርቱ ሊጠቀም እንደሚችል በጥናቱ የተካተተ ሲሆን ሰነዱም ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ስለመሆኑ የአስተዳሩ ከንቲባ ተናግረዋል፡፡
    ጥናት እቅራቢዎቹ በጥናታቸው ሶስት አማራጮችን ማቅረባቸውን ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ድሬዳዋን በሁለት ከተማ የሚያዋቅር ሲሆን ሁለቱን ከተማ ለማገናኘት በሚሰራው የመንገድ ዝርጋታ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ሁለተኛው አማራጭ በተበታተነ መልኩ ነዋሪው የሚሰፍርበት ከተማ የመመስረት ሲሆን ይህም በርካታ የመንገድ ስራ የሚጥይቅና ከፍተኛ ወጪ ያለው ስለመሆኑ እንዲሁም ሶስተኛው አማራጭ ድሬዳዋ አንድ ወጥ የሆነ ትልቅ ከተማ ሆና ህዝቡ በአግባቡ የሚጠቀምባቸውን መንገዶች በበቂ ሁኔታ የማዘጋጀትና የምንጠቀምባቸው የትራንስፖርት ዓይነቶች ምን መምሰል እንዳለባቸው በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
    በዚህም መሰረት አስተዳደሩ ሶስተኛ አማራጭ የተሻለ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለአጥኚው አካል ሀሳብ ያቀረበ ስለመሆኑ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ተናግረዋል፡፡ ስራው በቀጣይ ወደተግባር ሲገባ የመንገድ ዝርጋታ ስራው ኣራት ደረጃዎች እንደሚኖረውና መንገዶቹም የት ቦታ መሰራት እንዳለባቸው በጥናት አቅራቢው ቡድን በዝርዝር ጥናት ተደርጎና የትግበራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የሚቀርብና ዳግም ውይይት የሚደረግበት ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ የተጀመረው ስራም ድሬዳዋ በቀጣይ 20 ዓመት ከዕድገቷና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ሊፈጠርባት የሚችለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መጨናነቅ ለመቅረፍ የሚያስችል ስለመሆኑ ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡
    ከዚሁ ስራ ጋር በተያያዘ ቀደም ብሎ በአስተዳደሩ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት የገጠር ቀበሌዎችን ባካተተ መልኩ ድሬዳዋን በቀጣይ በአራት ክፍለ ከተማዎች የማደራጀትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታውንም በሁሉም አካባዎች በተገቢው ሁኔታ በማዳረስ ኢንቨስትመንቱ በነዚህ ቦታዎች ላይ የሚስፋፋና የህዝብ ቁጥሩን የሚሸከም ትልቅ ከተማ ለመመስረት እየተሰራ ስለመሆኑ የአስተዳደሩ ከንቲባው አቶ አህመድ መሐመድ ገልጸዋል፡፡