መቀመጫውን ድሬዳዋ ያደረገው ሬዳዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የኢንጅነሪንግ ክፍል ማናጀር ኢንጅነር ምንያህል ደበበ እንደተናገሩት ድርጅቱ በአሁን ሰአት የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን የኮቪድ 19 ወረርሽን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ፡፡
ድርጅቱ ወርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ከፍተኛ እጥረት የሚታይበትን ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ (መካኒካል ቬንትለት) በሀገር ወስጥ በራስ አቅም ለማምረት ሰፊ ግዜና በጀት መድቦ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ፤ከምግብ መድሀኒትና ቁጥጥር ባለስልጣን ፤ከአዲስ አበባ ፖሊ ቴክኒክና ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር ስራውን በጋራ ሲሰራ መቆየቱን ያወሱት ኢንጅነር ምንያህል በሂደቱ ሲሰጡ የነበሩ አስተያየቶች እየታረሙ በአሁን ሰአት ሰው ሰራሹ የመተንፈሻ መሳሪያ አገልግሎት መስጠት በሚያስችለው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢንጅነር ምንያህል ገለፃ መሳሪያው በአሁን ወቅት በአለም አቀፍ ገበያ አስከ 20 ሺ ዶላር የሚሸጥ ቢሆንም በአብዛኛው በሀገር ውስጥ ምርቶች ማሽኑን በ1ሺ 500 ዶላር ወጪ መስራት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ይሁንና ማሽኑን አገልግሎት መስጠት እንዲችል እና እየተቀጠፈ ያለውን የሰው ልጅ መታደግ እንዲቻል ለምግብ መድሀኒትና ቁጥጥር ባለስልጣን የማረጋገጫ ይሰጠን ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም ለጥያቄው ምላሽ ሳይሰጥ በመዘግየቱ ድርጅቱ በጉዳዩ ላይ ተስፋ መቁረጡን ተናግረዋል፡፡ድርጅቱ ማሽኑን በአገር ውስጥ አምርቶ ለገበያ የማቅረብ አላማ ሳይሆን የያዘው በሚቻለው መጠን ለህሙማን እንዲደርስ ለጤና ተቋማት የመለገስ እቅድ እንዳለው አያይዘው ጠቁመዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት አቶ አብሴራ ቡልቶ የአዲስ አበባ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ዲፓርትምት ከፍተኛ ባለሙያ በበኩላቸው መሳሪያው የመጨረሻውን ሙከራ ባለፊት ስምንት ቀናት ሳይቋረጥ ማከናወኑን አውስተው ሂደቱም ውጤታማ እና አመርቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ማሽኑ ወደ ስራ ለማስገባት የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም ባለሙያው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መሳሪያው ካለመብራት ለሰባት ሰአታት መስራት እንዲችል ባትሪ የተገጠመለት ስለመሆኑ ሲጠቀስ ድርጅቱ በቀን 150 ፍሬ ማሽኑን የማምረት አቅም እንዳለው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጻል፡፡
ማሽኑን ወደ ተጠቃሚ ለማድረስ እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽ በቀጣይ የምናቀርብ ይሆናል፡፡


