በአስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን ሁለገብ ሜዳ በተካሄደው የድጋፍ መርሀግብር ላይ ወ/ሮ ሜላት ብርሀኔ ማህበሩን በመወከል ባደረጉት ንግግር በአሜሪካና በአውሮፓ በሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆች የተመሰረተው ማህበር በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ሰብአዊ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል::
በዛሬው ድጋፍም ከተለያዩ የአስተዳደሩ የከተማ ቀበሌዎች ለተመረጡ 200 አቅመ ደካማ የእስልምና እና ክርስትና እምነት ተከታዮች በዓል መዋያ የሚሆን ለእያንዳንዳቸው 1ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉን ወ/ሮ ሜላት አስታውቀዋል::
“የድሬዳዋ ልጆች እና ወዳጆች አለምአቀፍ ማህበር” ከዚህ በፊት ለአስተዳደሩ ጤና ቢሮ የኮቪድ መመርመሪያ መሳሪያ በድጋፍ መስጠቱን እና በየአመቱ ለ100 ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ በመርሀ ግብሩ ላይ ተገልጿል::
ድጋፉ በተሰጠበት መድረክ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እና የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻኪር አህመድን ጨምሮ ሌሎች የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች የሀይማኖት አባቶች አርቲስቶች እና በድሬዳዋ የሚገኙ የማህበሩ አባላቶች ተገኝተዋል::
#ምንጭ የድሬዳዋ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት


