የተፈጠረውን የኦክስጂን እጥረት ለማቃለል ባለሀብቶች ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ተባለ፡፡

    በድሬዳዋ ጤና ቢሮ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ለሆነው የፈረንሳይ ሆስፒታል ክሮምቶ ማኑፋክቸሪንግ ፒልሲ 50 ኦክስጂን የተሞላባቸውን ሲሊንደሮች በድጋፍ አበርክቷል፡፡
    በድጋፍ አሰጣጡ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ዕለት ተዕለት የኮቪድ-19 ስርጭት መጠን መስፋፋቱን ተከትሎ በአስተዳደራችን የህሙማን ቁጥርም በመጨመሩ ምክኒያት የተከሰተውን የኦክስጂን እጥረት ግምት ውስጥ በማስገባት ክሮምቶ ማኑፋክቸሪንግ ፒልሲ ላደረገው የኦክሲጂን ሲሊንደሮች ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
    የተፈጠረውን የኦክሲጂን እጥረት ለማቅለል ሌሎች ባለሃቶች መሰል ድጋፎችን ሊያደርጉ ይገባልም ብለዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው ጨምረውም እየተስፋፋ ያለው የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ዝቅተኛ በመሆኑና ቸልተኝነት ስለሚታይ የወረርሽኙ መስፋፋት ስጋት እየፈጠረ መሆኑንና ህብረተሰቡ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የራሱንም የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ መንግስትም ሆነ የጤና ባለሞያዎች ወረርሽኙን ለመከላከልና በኮቪድ ምክኒያት የሚያልፈውን ህይወት ለማዳን የሚያደርጉትን ግብግብ በመረዳት ሊያግዝ ይገባል ብለዋል፡፡
    የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው ክሮምቶ ማኑፋክቸሪንግ ፒልሲ ከዚህ ቀደምም ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚሰሩ ሥራዎችን ሲደግፍ እንደነበርና አሁንም ያለውን የኦክሲጂን ሲሊንደርና የኦክስጂን እጥረት አይቶ በ450‚000 ብር ኦክስጂን የተሞላባቸው 50 ሲሊንደሮችን ገዝቶ በድጋፍ መስጠቱ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊዋ አያይዘውም አሁን ያለውን የኦክስጂን እንዲሁም የመድሃኒቶች እጥረት በመንግስት አቅም የሚሸፈን ባለመሆኑ በአስተዳደሩም ይሁን በሌላ ሥፍራ የሚኖሩ ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበው ህብረተሰቡ ቀጣይ የሚከበሩ የሁለቱንም ሃይማቶች በዓላት ተከትሎ የኮቪድ-19 መመሪያን ግምት ውስጥ ባላስገባ ሁኔታ መሰባሰቡን በመግታት የራሱንም ሆነ የሌሎችን ህይወት ከወረርሽኙ ሊከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
    የክሮምቶ ማኑፋክቸሪንግ ፒልሲ ስራ አስኪያጅ አቶ አበባው መኮንን ፒልሲው የህብረተሰቡ መሆኑንና ህብረተሰቡ የሚደርስበት ማንኛውም ችግር የፒልሲውም ችግር በመሆኑ አሁን ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በቀጣይ ክፍተቶች እየታዩ ድጋፎች የሚቀጥሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
    በድሬዳዋ ጤና ቢሮ የፈረንሳይ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል አስተባባሪ አቶ ትዕግስቱ የማነ የህክምና ማዕከሉ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ያለው የኦክስጂን እጥረት ተግዳሮት እንደሆነበትና ይህንን ግምት ውስጥ አስገብቶ ፒልሲው ድጋፍ ማድረጉ የሚያስመሰግነው ሲሆን የህክምና ማዕከሉ በቀን ከ80-90 ሲሊንደሮችን እደሚጠቀምና ካለው እጥረት የተነሳ የታማሚዎች ህይወት እያለፈ መሆኑንና ይህንኑ ችግር ለመቀነስ ሌሎችም ባለሃብቶች የክሮምቶ ማኑፋክቸሪንግ ፒልሲ አርዓያን በመከተል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
    አስተባባሪው ጨምረው እንዳሉት ለህክምና ማዕከሉ የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን ከነዚህ ድጋፍ አድራጊዎች መካከል ጃሌ ድሬ የባህል ምግብ ቤት እና የኦክስጂን አቅራቢ የሆኑት አቶ ዘይኑ በህክምና መስጫ ማዕከሉ የሚሰሩ ሙስሊም እህት ወንድሞቻችንን ለማስፈጠር እንዲሁም ቢጂ አይ ኢትዮጲያ 30 ሳጥን ስንቅ ከአልኮል ነፃ መጠጥ ስላበረከቱልን በዚህ አጋጣሚ በጤና ባለሞያዎችና በድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
    ምንጭ፦ ድሬዳዋ ጤና ቢሮ