በሁሉም ከተማ ቀበሌዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአስተዳደሩ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

    ከ2014-2016ዓ.ም የድሬዳዋ ከተማ የካፒታል ኢንቨስትመንት ዕቅድ (CIP)ዝግጅት አስመልክቶ የከተማው ህብረተሰብ እና የባለድርሻ አካላት ጋር በእቅድ ዝግጅቱ እንዲካተቱ የሚያስፈልጉና አዲስ ኘሮጀክቶች ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡ ፡
    በአስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች ከፕሮጀክቶቹ መካከል ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥረው የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራን ጨምሮ የጠጠር መንገድ፣ የጎርፍ መከላከያ ግንብ፣ አዲሱ ቄራ፣ የመንገድ መብራት፣ ፓርክና የመንገድ አካፋይ ግንባታና አረንጓዴ ልማት ስራዎች፣ እንዲሁም አቅም ግንባታና እቃ ግዢ እና የተለያዩ ጥናቶችን ማስጠናት ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ የከተማ ስራ አሲኪያጅ ጽ/ቤት የፕላንና በጀት አሳታፊ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኤፍሬም ተስፋዩ ተናግረዋል ፡፡
    አቶ ኤፍሬም ከዚህም ጋር አያይዘው ላለፉት ዓመታት የከተማ መሰረተ ልማት ፕሮግራም በሚል በተቋቋመበት ወቅት በርካታ መሰረተ ልማቶችን ለከተማዋ ያስገነባ እንደሆነና አሁን የከተማ መሰረተ ልማትና የተቋም አቅም ግንባታ ፕሮግራም በሚል አዲስ ስያሜ ተደራጅቶ በተጠናከረ መልኩ የከተማዋን ገጽታ ለመለወጥ እየሰራ እንደሆነ በመግለፅ በቀጣይ የአስተዳደሩ አመራሮች አንደሚወያዩበትም ገለፃል ፡፡
    በፕሮጀክት ግምገማው የተሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች ተቋሙ ከአመት አመት አፈጻጸሙ እየተሻሻለ መምጣቱ እና አሳታፊነቱ የሚያስመሰግን መሆኑን በአጽንዖት የተናገሩ ሲሆን የግንባታዎች መጓተት፣ በተለይ በ03 ቀበሌ የወጣት ማዕከል ግንባታ፣ የከባድ ተሸከርካሪዎች ለረጅም ጊዜ በመቆም በኮብል ስቶንና በአስፋልት መንገዶች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት፣ በአዲስ የጉዞ ለውጥ የተደረገበት የሰኢዶ መንገድ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ለድምጽ ብክለት እና ህጻናቱንም ለትራፊክ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ፣ የከተማ ውስጥ ጋራዦች፣ በልማት የማይካተቱ መንደሮችን ትኩረት እንዲሰጥ፣ ከዋና ዋና መንገዶች ውጪ ያሉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መብራት ትኩረት እንዲሰጣቸው፣ የከተማዋ ፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት፣ የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት፣ ጽዳት፣ ፍትሀዊ የልማት ክፍፍል ጥያቄዎች በመድረኩ ከተሳታፊዎች የተነሱ አስተያየቶች ናቸው፡፡