ፖሊስ ኮሚሽኑ ከምን ጊዜውም በላይ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ በመስራት ላይ እንደሚገኝም ተገልፆል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና እምነት ተከታዮች በጋራ በአንድነት ተቻችለውና ተከባብረው እንደሚኖሩባት ይታወቃል ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የከተማዋን በጋራ የመኖር እሴትን ለማደፍረስ የሚጥሩ ፀረ-ሰላም ሀይሎች ወደ ከተማዋ እንደገቡ ተደርጎ ያልተጨበጡና ፍፁም ከእውነት የራቁ መረጃዎችን ህብረተሰቡ ዘንድ እየተሰራጩ ይገኛሉ ። እነዚህም መረጃዎቹ ፍፁም ከእውነት የራቁና ከተማዋ ከምን ጊዜውም በላይ ሰላሟ የተረጋገጠች ከተማ እንደሆነችና ነዋሪውም በነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች መረበሽ እንዳማይገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረዋል ።
ኮሚሽነር አያይዘውም ከምርጫው ጋር ተያይዞ አራት ወንጀሎች ማጋጠማቸውን ገልፀው የምርጫውም ሂደት ሰላማዊ በሆነ አግባብ ይከናወን ዘንድ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝና በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረው የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽንም ከሌላው ጊዜ በተጠናከረ መልኩ ሰላምን ለማረጋገጥ እራሱን ዝግጁ እንዳደረገና በቀጣይ ቀናት ለሚከበሩ በአላትም በሰላም ይከበሩ ዘንድ ዝግጅት መደረጉን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረዋል ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማችን ድሬዳዋ ላይ እየተስተዋሉ ከሚገኙ ህገ-ወጥ ንግዶች እንዲሁም በእግረኛ መንገዶች ላይ በህገ-ወጥ መንገድ የተሰሩ የተለያዩ የንግድ ቤቶች ላይ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ምክትል ስራ አስኪያጅና የደንብ ማስከበር ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ነጂብ ኢድሪስ እንዳሉት እነዚህ ችግሮች በስፋት እንደተበራከቱና በቀጣይም ህጋዊ የሆኑ እርምጃዎች የመውሰዱ ስራ እንዲሰራ ተናግረው ቀጣይ ቀናት የበአል ቀናት እንደመሆናቸው መጠን ህገ-ወጥ የሆነ እርዶችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በትኩረት እንዲሰራም ነው አቶ ነጂብ የተናገሩት ።
በከተማችን ላይ ከበአላት ጋር ተያይዞ የዋጋ ምርቶች ጭማሪዎች ይስተዋላሉ ይህንንም ከመከላከል አኳያ የቁጥጥር ስራዎችን ከመስራት ባለፈ የአቅርቦት እጥረት እንዳይኖርም ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ አብዲ ሙክታር ተናግረው ከዚሁ ጋር ተያይዞም የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ምርቶችን በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይም እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል ።


