በቀበሌ 06 አስተዳደር 200 ለሚሆኑ ችግረኛ ነዋሪዎች ድጋፍ ተደረገ::

    የቀበሌ 06 አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም በአካባቢው ላይ ለከተማ ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎች በቀበሌው ከሚገኙ ባለሀብቶችና የንግድ ማህበረሰቦች ባሰባሰቡት ገንዘብ 200 ለሚሆኑ ለአካባቢው ችግረኞች የታለቁን ረመዳን ጾምና የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በድጋፍ መድረኩ ላይ የአስተዳደሩ ም/ከንቲባና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲን ወክለው ለከተማው ምክር ቤት የሚወዳደሩ አመራሮች በተገኙበት የድጋፍ ስነ-ስርዓቱ ተካሂዷል፡፡
    ድጋፉ የድሬዳዋ ነዋሪዎችን የመቻቻል፣ የመደጋገፍና የመተባበር ብሎም በፍቅር እብሮ የመኖር እሴት የሚያጎለብት መሆኑን የአስተዳደሩ ም/ከንቲባና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ከድር ጁሀር የገለጹ ሲሆን በሌሎች አካባቢዎችም አሁን ካለው የኮሮና ቫይረስ ጫና አንጻር ችግረኛ ለሆኑ አካላት ተመሳሳይ ድጋፎች ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ድጋፉ እንዲከናወን እገዛ ላደረጉ የንግዱ ማህበረሰብና ባለሀብቶች ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡
    የቀበሌ 06 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዚያድ መሐመድ እንዳሉት ድጋፉ ትኩረት ያደረገው የምግብ ዋስትናን ጨምሮ በተለያዩ የድጋፍ ማእቀፍ ውስጥ ያልተሳተፉ አቅመ ደካማ የሆኑ፣ ወላጆቻቸውን ያጡና በህመም ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኙ የቀበሌው ነዋሪዎችን የቀበሌው አመራር በሚደግፈው ቀጠና የመለየት ስራ የተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ድጋፉ ከ300,000.00 (ከሶስት መቶ ሺህ ብር) በላይ የጠቆሙ ሲሆን ድጋፉም ችግር ውስጥ የሚገኙ አካላት ችግርን በጊዜያዊነት የሚቀርፍ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
    ድጋፍ የተደረገላቸው ነዋሪዎችም በዚህ መልኩ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑ በጊዜያዊነት ችግራቸውን ለመፍታት የሚስችል መሆኑን ጠቁመው ድጋፍ ላደረገላቸውም አካል ምስጋናቸውን አቅረበዋል፡፡ አያይዘውም በቀጣይ ተመሳሳይ ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል፡፡