ነዋሪው ህብረተሰብም ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ተገልፃል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት በከተማችን ድሬዳዋ ብሎም በአጎራባች ክልሎች አደጋ ከመድረሳቸው አስቀድሞ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ለአደጋው ቅድመ መረጃ ኖሯቸው ለአደጋው ተጋላጭ እንዳይሆኑ ብሎም ሊደርስ ከሚችል ጉዳት እራሳቸውን እንዲከላከሉ ተገቢውን መረጃ ይሰጣል ።
ከዚህም ባለፈም ይህንን ስራ ለሚሰሩ አስፈፃሚ ሴክተር መስሪያ ቤቶች መረጃውን ተንተርሰው አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን እንዲሰሩ መረጃውን የመስጠቱን ስራ ከመስራት ባለፈ ድንገት አደጋው ቢከሰት ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ስራዎችንም ፅህፈት ቤቱ ይሰራል ።
ይህንንም ተከትሎ የድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ የምስራቅ ሀረርጌ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ሶስት ቀናት ከፍተኛ የሆነ ዝናብ በተመሳሳይ ሰአት እንዲሁም በተለያየ ሰአት ሊጥል እንደሚችል የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ባደረሰው ትንበያ መሰረት በነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ከፍተኛ ባለሞያ የሆኑት አቶ ሸምሸዲን መሀመድ ተናግረዋል ።
አቶ ሸምሸዲን አክለውም በተለይም የድሬዳዋ አስተዳደር ለጎርፍ ተጋላጭ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ እንዲሁም በምስራቅ ሀረርጌ አካባቢዎች ላይ የሚዘንበው ዝናብ ጎርፍ ሆኖ ከተማችን ድሬዳዋ ላይ የመምጣት እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ነዋሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው አቶ ሸምሸዲን የተናገሩት ።


