በመላ ድሬዳዋ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ ዕለተ ስቅለት በድምቀት ተከበረ::

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የካቲት መጨረሻ ላይ የተያዘው የአብይ ጾም በጾምና በጸሎት አምላክን በመለመንና በመማጸን አሳልፈው ጾሙ ሊገባደድ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ በተለይም በአብይ ጾም የመጨረሻው አርብ ከሌላው ቀናት ለየት የሚያደርገው ኢየሱስ ክርስቶች በመስቀል ላይ እሱ ሞቶ ለመላ የሰው ልጆች ህይወት የሰጠበት ዕለት በመሆኑ ቀኑን በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ይከበራል፡፡ ስለሆነም ይህን በማሰብ በመላ ድሬዳዋ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ የስቅለት ቀንን በድምቀት ተከብሯል፡፡
    በድሬዳዋ ደብረሰላም መድኃኒዓለም ካቴድራል ተገኝተው የስቅለት ዕለትን ያሳለፉት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ልዩ ጽ/ቤትና የውጪ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የድሬዳዋና የጅቡቲ ሀገረስብከት ሊቀፓፓስ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ እንዳሉት የስቅለት ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመገረፍ፣ በመስቀል ላይ በመቸንከርና የሾህ አክሊል በመድፋት ለሰው ልጆች ሲል ሞቶ ህይወት የሰጠበት በመሆኑ የመከራ ፍጻሜና የድህነት ዕለት ናት ስለሆነም ከሌሎች ዕለቶች ለየት ያደርጋታል ብለዋል፡፡ ይህንንም በማሰብ ዕለቱን በጾም፣ በጸሎትና በስግደት አምላክን በመለመንና በመማጸን በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚያልፍ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
    የስቅለት ቀን ለሰው ልጆች ድህነትን፣ ፍቅርን ሰላምንና ይቅርታን አምላክ ያደረገበት ዕለት በመሆኑ ዕለቷ ፍጹም የድህነት መልካም ቀን ተብላ እንደምትጠራም ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ገጸዋል፡፡ የሰው ልጆች ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በዕዳና በፍዳ የተያዙበትንና በዚህ ዕለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የዕዳ ደብዳቤውን የቀደደበትና ያስወገደበት ስለሆነ ዕለቱ ለየት የሚል ስለመሆኑም አክለው ጠቁመዋል፡፡ ክርስቶስ በደረሰበት መከራና ስቃይ ለሰው ልጆች ፍጹም ፍቅሩንም የገለጸበት ዕለትም ነው በማለት ተናግረዋል፡፡ በሌላ መልኩ ዕለቱ የሰቀሉትን፣ የቸነከሩትን፣ ጎኑን የወጉትንና የእሾህ አክሊል የደፉበትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ምህረት የሰጠበት ዕለት ነው በማለት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ተናግረዋል፡፡
    ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ከስቅለት ለሰዎች መራራትን፣ ማዘንን፣ ይቅርታ ማድረግን፣ ፍቅር መለገስንና ሰላም መስጠትን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማርን በመሆኑ ስቅለትን ስናስብ ረዳት ለሌላቸው፣ በችግር ምክንያት ለተራቆቱ፣ ለገረጡና ለከሱ መርዳት እንዳለብን እንረዳለን ብለዋል፡፡ በሌላ መልኩም ይቅር ማለትን ከስቅለት ዕለት የምንማር በመሆኑ ይቅር መባባልና ምህረት ማድረግ ለሀገራችን ህዝቦች በሙሉ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የትንሳኤ በዓልንም ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ በጎ ነገርን በማድረግ ልናከብር ይገባል ብለዋል፡፡ ችግረኞችን በመደገፍና በመርዳት በዓሉን ማክበር ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሳው ክርስቶስን ማሰብ ነው በማለትም ጠቁመዋል፡፡
    በዓሉን ስናከበር ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ልናደርግ እንደሚገባና የሚሰጡ ሙያዊ ምክሮችን በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ገልጸዋል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ክትባት ጋር በተያያዘም ከእምነቷ አስተምህሮ ጋር የማይጋጭ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ክትባቱን የማግኘት ዕድል ሲገጥማቸው በመከተብ እራሳቸው ከቫይረሱ ሊከላከሉ ይገባል ብለዋል፡፡
    ያነጋገርናቸው የእምነቱ ተከታዮችም በጾም፣ በጸሎትና በስግደት እንዲሁም ከኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ዕለተ ስቅለትን እያሳለፉ መሆኑን ጠቁመው የፋሲካ በዓልን ስናከብር በመረዳዳት በመደጋገፍና ለተቸገሩ አስፈላጊውን ሁሉ በመለገስና ያለንን በማካፈል ልናከብር ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም የሁሉም እምነት ተከታዮች ለሀገራችን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ልንጸልይ ይገባል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብና ለእምነቱ ተከታዮችም በዓሉ መልካም እንዲሆን ያላቸውን ምኞታቸውን ገልጸዋል፡