ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል አረጋዊያንን ታሳቢ ያደረገ የበጎ አድራጎት ተግባር ማከናወን እንደሚገባ ተገለፀ::

    የድሬዳዋ ዳያስፖራ ማህበር በዳዊት አረጋውያን መርጃ ማህበር ለታቀፉ አረጋውያን መሳ የማጋራት ፕሮግራም አካሂዷል።
    በምሳ ማጋራት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሐር አረጋዊያን የሀገር ሀብት መሆናቸውን ገልፀው ሁሉም ማህበረሰብ አረጋዊያንን ታሳቢ ያደረገ የበጎ አድራጎት ተግባር ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል።
    አስተዳደሩ የአረጋዊያንን ኑሮ የሚደግፉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ምክትል ከንቲባው ለዳዊት አረጋውያን መርጃ ማህበር ማዕከል መገንቢያ መሬት በመስጠት የማእከሉ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን አስረድተዋል ።ግንባታው እስኪጠናቀቅ አስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
    በሌላ በኩል አቶ አክሊለ ታጠቅ የድሬዳዋ ዲያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር የዲያስፖራው ማህበሩ በድሬደዋ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እያከናወኑ ካለው ዘርፈ ብዙ ስራ በተጨማሪ በበጎ አድራጎት ስራላይም በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።ይህንን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።በዳዊት አረጋውያን መርጃ ማህበር ላካሄዱት መሳ የማጋራት ፕሮግራም አመስግነዋል።
    የድሬደዋ ዲያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ነጂሐ አህመድ ማህበራቸው ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን በጎ አድራጎት ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥል ገልፀው ዳዊት አረጋውያን መርጃ ማህበር እየገነባ የሚገኝውን ማዕከል እስከ ፍፃሜው በማንኛውም መልኩ እንደሚደግፍ ጠቁመዋል።