ህይወታቸውን መቀየር እንዲችሉ የተመቻቸውን የሙያ ስልጠና የወሰዱ ጎልማሳ የጎዳና ተዳዳሪዎች በዛሬው ዕለት ተመረቁ::

    በአስተዳደሩ በጎዳና ላይ ኑሮዋቸውን ይመሩ የነበሩ ጎልማሶች በስደስት የተለያዩ የሙያ መስኮች ለአምስት ወራት ስልጠና ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡ ስልጠናው የድሬዳዋ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ከሀረርጌ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር ጎዳና ላይ ይኖሩ የነበሩ አካላትን በመመልመል የተለያዩ ሙያዊ ስልጠና እንዲያገኙ በማመቻቸት የእራሳቸውን ህይወት የሚለውጡበት ሁኔታ ዓላማ ያደረገ መሆኑን የገለጹት የድሬዳዋ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ሸርማርኬ መሐሙድ ናቸው፡፡ ስልጠናው የወሰዱ አካላትም ወደቀድሞ ህይወታቸው እንዳይመለሱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ወደስራ የማስገባት ስራ ለመስራ የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው አያይዘውም የአስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ሌሎች በተለያዩ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ አካላትን ከችግራቸው በማላቀቅ እራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ ለመፍጠር በርካታ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
    የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ አሰሪና ሰራተኛ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መሐመድ ኢብራሂም በተቋሙ ለረጅም ጊዜ ጥናት በማድረግ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ጎልማሶችን ከተረጂነት ለማውጣት ታቅዶ የተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን በተለያዩ ማህበራዊ ችግር ምክንያት ጎዳና ላይ ኑሮዋቸውን ያደረጉ አካላትና ህይወታቸውን ለማሻሻል ዝግጁ የሆኑ ጎልማሶችን በሀረርጌ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ተመልምለው ለ3 ወር የስነ ልቦና ስልጠና እንዲያገኙ ከተደረገ በኋላ ሁሉም እንደየፍላጎቱ የእንጨት ስራ፣ የጂፕሰም፣ የብየዳ ስራ፣ የባንቧ ስራ፣ የሴራሚክ ስራ እና የልብስ ስፌት የሙያ ስልጠና በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋም ስልጠና እንዲያገኙ መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ አካላት በዚህ መልኩ ስልጠና ማግኘታቸው በቀጣይ የራሳቸው የሆነ ገቢ ማግኘት እንዲችሉ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም በዘለለ ቀደም ብሎ ለመንግስት የልማት ጉዞ አቅም ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡
    በሀረርጌ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማህበረዊ ልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ወክሎ የተናገሩት መርሴ ሀዘን ጥላሁን እንዳሉት ተቋማቸው 250 የሚሆኑ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ጎልማሶችን በተለያዩ ሙያ ለማሰልጠን ከአስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር የሁለት ዓመት ስምምነት የተፈራረሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ ስልጠናም የዚህ ስምምነት አካል ሲሆን በመጀመሪያ ዙር 120 ጎዳና ላይ የሚኖሩ ጎልማሶችን ለአምስት ተከታታይ ወራት የስነ- ልቦናና የተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎች እንዲያገኙ በማመቻቸት ማስመረቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
    በስልጠናው ተሳታፊ የሆኑ አካላትም ስልጠናው ከጎዳና ህይወት እራሳቸውን በማውጣት አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ያሉ ሲሆን በቀጣይ ወደስራ ገብተው የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡