ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የሁለቱን ቋንቋዎች የፅሁፍ ፈተናዎች የትርጉም ስራ ከድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ተረክቧል፡፡
በርክክብ ስነስረአቱ ላይ የትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰአዳ አዋሌ እንደተናገሩት በጽ/ቤቱ ከዚህ ቀደም የእጩ አሽከርካሪዎች የፅሁፍ ፈተና ይዘጋጅ የነበረው በአማርኛ ቋንቋ ብቻ መሆኑን ተከትሎ በርካቶች ፈተናውን ተረድቶ ከመስራት አንፃር ሰፊ ክፍተት እንደነበር አስታውሰው በዚህም በተለይ የተግባር ፈተናውን ባግባቡ የሰሩ እጩ አሽከርካሪዎች የፅሁፍ ፈተናውን ባግባቡ ባለመረዳታቸው ፈተናውን ለማለፍ ይቸገሩ እንደነበር ነው የገለፁት፡፡
ይህንኑ መነሻ በማድረግ በማህበረሰቡ ጥያቄ መሰረት ተቋሙ የፅሁፍ ፈተናውን ከአማርኛ በተጨማሪ ለኦሮመኛና ሱማለኛ ተናጋሪዎች በቋንቋቸው እንዲዘጋጅላቸው ከድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ጋር በተደረገ ስምምነት የትርጉም ስራው አልቆ በእለቱ ለርክክብ በቅቷል ብለዋል፡፡
እንደተቋምም ፕሮግራሙን በአጭር ጊዜ በመጫን ወደ ስራ እንዲገባ ይሰራልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በእለቱ ለዚህ ስራ መሳካት ጥረት ያደረጉትን አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲዎች ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ በማህበራዊ አገልግሎት ላይ የመሳተፍ ኃላፊነትን አንግበው እንደ መቋቋማቸው በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቀረበልን ጥያቄ መሰረት በኦሮመኛና ሱማለኛ ቋንቋ የእጩ አሽከርካሪዎችን የፅሁፍ ፈተና ትርጉም በማሰናዳት ለእለቱ ርክክብ አብቅተናል ብለዋል ፡፡
በዚህ ተግባር ላይ በመሰማራታችንም ትልቅ እርካታ ይሰማናልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ከትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር ያለንን ትስስር በማጠናከር የማህበረሰቡን ችግር ሚፈቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመስራት እቅድ ይዘናልም ብለዋል፡፡
ከተቋሙ በተገኘው መረጃ የትርጌም ስራው በማለቁ በአጭር ጊዜ ወደ ሰርቨር በመጫን ከአመርኛ በተጨመሪ በሶማልኛና በአሮመኛ ቋንቋ የጽሁፍ ፈተናውን ለመስጠት ይሰራል ተብሏል፡፡
ምንጭ፦ Federal Transport Authority Dire Dawa Branch


