8ኛው # የብስክሌተኞችና # የእግረኞች ቀን መርሀግብር ድሬደዋ ላይ በተለያዩ መርሀግብሮች በድምቀት ተከብሯል፡፡

    አሽከርካሪዎችም ሆነ ተሳፋሪዎች ራሳቸውን ከትራፊክ አደጋ መጠበቅና በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ ማስክን ባግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡
    ወር በገባ የመጨረሻው እሁድ ሚከበረው የሞተረ አልባ ተሽከርካሪዎችና የእግረኞች ቀን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ድሬደዋ ላይ ተከብሯል፡፡
    በስነስረአቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰአዳ አዋሌ እንደተናገሩት ማህበረሰቡ አማራጭ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችንና የእግር ጉዞ ባህልን እንዲያጎለብት ገንዛቤን በመፍጠር እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ታስቦ መርሀግብሩ በትራንስፖርት ሚኒስትር እና በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ትብብር ወር በገባ የመጨረሻው እሁድ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል፡፡
    በዚህም በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤን ለመፍጠር መቻሉንና ለውጦችም እየታዩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
    ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም አሁን ላይ ከምንግዜውም በላይ ስርጭቱ እየጨመረ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ ሌላ ስጋት ሌላ ፈተና ሀኗል ያሉ ሲሆን በተለይ ማህበረሰቡ ትራንስፖርትን ሲጠቀምም ሆነ አሽከርካሪው ሲያሽከረክር ማስክን ባግባቡ በመጠቀም ራሱን ከቫይረሱ እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
    ይህን ለመከላከል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የመንገድ ላይ ቁጥጥርን በማጠናከር ማስክ በማይለብሱና ያለማክስ ያለ ተሳፋሪን ጭነው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ በወጣው ህግ መሰረት ጠበቅ ያለ የቅጣት እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል፡፡
    በትራንስፐፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ጉልማ ታዬ በመድረኩ ላይ ማህበረሰቡ በትራፊክ አደጋ እንዳይጎዳ ህግን አክብሮ መንገዱን ባግባቡ እንዲጠቀምና የሞተር አልባ ተሽከርካሪንና የእግር ጉዞን ባህል እንዲያደርግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
    በመድረኩ ላይም የትራፊክ አደጋን አስከፊነትና የኮሮና ወረርሽኝን አስቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮሩ መልእክቶችም ተላልፈዋል፡፡
    በእለቱ በተመረጡ ጎዳናዎች ላይ በእለቱእንግዶችና በማህበረሰቡ የሳይክልና እግር ጉዞ በማካሄድ መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡