በሀገር ጉዳይ ላይ አንድ አይነት አቋም በመያዝ በጋራ መሰለፍ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር አስታወቁ ።

    የሰላም ሚኒስቴር ከድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ 9 የከተማ እንዲሁም በ 38 ገጠር ቀበሌዎች ላይ በሚገኙ አካባቢዎች የሰላም ሚኒስቴር ባለሞያ በመመደብ ያለፍትን አራት ወራት ህብረተሰብ ተኮር የሆኑ ውይይቶች እንዲሁም የግለሰብ ችግር ፣ የአካባቢ ችግር ፣ የማህበረሰብ ችግር ፣ የአስተዳደር ችግርና የፌደራል ችግር በማለት ባሉት አጠቃላይ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል ።
    በተለይም ህብረተሰቡ በሚኖርባቸው አካባቢዎች በፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ እንደዚህ አይነት ውይይቶች መደረጋቸው ለአካባቢው ብሎም ለአስተዳደሩ ሰላም መረጋገጥ አይነተኛ አስተዋፆ እንደሚኖረው ይታመናል ። ባለፍት አራት ወራትም በገጠርና በከተማ የተካሄዱት የማህበረሰብ ተኮር የፀጥታ ውይይቶች አስመልክቶ በምክር ቤት አዳራሽ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል ።
    በውይይቱ ላይም በክብር እንግድነት የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር የሰላም እሴት ግንባታችንን ለማጠናከር ሁላችንም ያለሰለሰ ጥረት በማድረግ በአንድነት በመሆንና ሀገራችን ኢትዮጲያን ለየትኛውም ሀገር አሳልፈን መስጠት እንደማይገባ ተናግረው በሀገር ጉዳይ ላይ አንድ አይነት አቋም በመያዝ በጋራ መሰለፍ እንደሚገባም አቶ ከድር ተናግረዋል ።
    ህብረተሰቡ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የፀጥታና የሰላም ውይይቶች መካሄዳቸው በተለይም ቀላል የሆኑ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ከመቅረታቸውም በዘለለ በየአካባቢው ይከሰቱ የነበሩ ሁለቶችና ግጭቶች እንደቀነሱና ከፖሊስ ጋር በመሆንም በርካታ የፀጥታ ስራዎች መሰራታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ የሰላም እሴት ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኢብሳ አሜ ተናግረው በቀጣይም አስተዳደሩና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በጋራ መስራት እንደሚገባም አቶ ኢብሳ አሜ ተናግረዋል ።