1442ኛው የሸዋል ኢድ በዓል በድሬደዋ የሐረሪ ብሄረሰብ ተወላጆች በዛሬው እለት በድሬደዋ ሚሊኒየም ፓርክ በድምቀት ተከብሯል፡፡
ከታላቁ የረመዳን ፆም ፍቺ አምስት ቀናት በኋላ ተከብሮ የሚውለው ሸዋል ኢድ በሐረሪ ብሄረሰብ ዘንድ በድምቀት እንደሚከበር የገለጹት በድሬደዋ የሃረሪ ኮሚዩኒቲ አስተባባሪ አቶ ዜዳን በክሪ በዓሉ በብሄረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡በዓሉን በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው አቶ ዜዳን የገለፁት፡፡
አቶ ዜዳን አክለውም ከክልሉ ውጪ ያሉ የብሄረሰቡ ተወላጆን በተመለከተ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ማግኝቱ የብሄረሰቡ ተወላጆች በአገሪቱ ፖለቲካ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያረጋገጠ ሆኗል ብለዋል፡፡
በቀጣይ በሃረሪና በድሬደዋ መካከል ያለውን የወንድማማችነት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የበለጠ በማዳበር የሐረሪ ብሄረሰብ ተወላጆች በድሬደዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እረገድ እያበረከቱት ያለውን አስተዋፆ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ዜዳን በክሪ አረጋግጠዋል፡፡
በስነስረአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በድሬደዋና በሃረሪ ክልል ለአመታት የዘለቀ የዳበረና የጠነከረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መኖሩን ገልፀዋል፡፡የሃረሪ ብሄረሰብ ቋንቋ የሆነው አደሪኛ በድሬዳዋ በተለይ በአንዳንድ የከተማው ክፍሎች ከሌሎች ቋንቋዎች እኩል ለመግባቢያነት እንደሚውል የጠቀሱት አቶ ከድር ይህ ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የብሄረሰቡ ተዋላጅ ባለሃብቶች በድሬደዋ ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት አስተዳደሩን እና ነዋሪችን ተጠቃሚ እያደረጉ የሚገኙ የልማትስ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙም ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡ወደፊትም ሃረሪዎች ድሬደዋን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው በማየት በድሬደዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በሐረሪ ብሄረሰብ ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የሸዋል ኢድ በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካት የድሬደዋ አስተዳደር አስከመጨረሻው ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ከድር ጁሃር አረጋግጠዋል፡፡
በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ በተከበረው በዚህ በዓል ላይ የሃማኖት አባቶች ኡጋዞችና የሃገር ሽማግሌዎች የታደሙ ሲሆን ከሃረሪ ክልል ና ከድሬደዋ አስተዳደር ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የድጋፍ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡


