ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሀገራችን ኢትዮጲያ እያከናወነችው ባለችው የልማትና የህግ-ማስከበር ስራዎች ብሎም የውስጥ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የውጪ ሀገራት ጣልቃ መግባታቸውን አስመልክቶ ” ድምፃችን ለነፃነታችን ” በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ወጣቶች አውግዘዋል ።
ኢትዮጲያዊያን በሀገር ጉዳይ የማንደራደር ሀገር ወዳድ ህዝቦች እንደመሆናችን መጠን ለነፃነታችን የውጪ ጣልቃ ገብነትን በመቃወምና በአንድነት በመሆን በሀገራችን ላይ የተቃጣውን እኩይ ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
በዛሬው እለት የሀገራችን ብሎም የአስተዳደሩ ወጣቶች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ከሀገራቸውና ከመንግስታቸው ጎን ለመቆም በአደባባይ በመውጣት ድምፃቸውን ለአለም በማሰማት የሀገራቸውን ነፃነት ለአለም ያሳዩበት መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ተናግረዋል ።
ታላቁ የሀገራችን ህዳሴ ግድብ ከመሞላቱ በዘለለ 6 ተኛው ሀገራዊ ምርጫም ያለ ምንም ችግር እንደማይደናቀፍና በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ማንም ጣልቃ እንዲገባ አንፈቅድም በማለት ድምፃችንን በአንድነት ማሰማት እንደሚገባ የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ መብራቴ ገብረየስ ተናግረዋል ።
ወጣቶች ከምንጊዜውም በላይ አንድነታቸውን በማጠናከር የሀገራችንን የብልፅግና ጉዞ ለማስተጓጉል የሚጥሩ የተለያዩ የውጪ ሀገራትን በጋራ በመሆን መቃወም እንደሚገባ በእለቱ ተሳታፊ የሆኑ በአስተዳደሩ የሚገኙ ወጣቶች ተናግረዋል ።
በንቅናቄ ፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይም የውጪ ጣልቃ ገብነትን አስመልክቶ የአስተዳደሩ ወጣቶች ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ ከማውጣታቸውም በዘለለ በሀገራዊ ጉዳይ በጋራ ፣ በአንድነት ፣ በመተባበርና በመተጋገዝ እንዲሁም ለሀገራችን ልማትና ብልፅግና በጋራ መቆምን የሚያወድሱ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ በሰልፍ ላይ ታድመዋል ።


