በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በፅንፍኛው የህወሀት ጁንታ ቡድን ላይ መንግስት ባስቀመጣው አቅጣጫ መሰረት ህግን የማስከበር ግዳጅ ላይ በላቀ ወታደራዊ ዝግጁነትና ጀግንነት ፈፅመው የተመለሱ በኢ.ፌ.ድ.ሪ አየር ሀይል የምስራቅ አየር ምድብ አባላት የጀግና አቀባበል ከማድረግ ባለፈ የእውቅና ሽልማትና የማእረግ ማልበስ መርሀ-ግብር ተካሄዷል ።
በኢ.ፌ.ድ.ሪ አየር ሀይል የምስራቅ አየር ምድብ በበጀት አመቱ በግዳጅ አፈፃፀም ፣ በፈጠራና ሞዲፊኬሽን ፣ በስልጠና ጥገና በወታደራዊ ዲሲፒሊን በመልካም አስተዳደር ግንባታ ውጤታማ በሆነ መልኩ ላከናወኑ ዩኒቶች አካላትና ሰራተኞችም የምስጋና እንዲሁም እውቅና ሽልማት ለአየር ሀይል አባላት ተሰጥቷል ።
በእለቱም በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ድ.ሪ አየር ሀይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢ.ፌ.ድ.ሪ አየር ሀይልና ሰራዊት አባላት ግዳጅ ሰፊ ከመሆኑ ባለፈ በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቅና ቢሆንም ግን አሁን ላይ የተጀመሩትን አጠቃላይ የምድቡን ዝግጁነት በማረጋገጥ ለማንኛውም ግዳጅ ሰራዊታችንና ጀግኖቻችንን ማዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የኢ.ፌ.ድ.ሪ አየር ሀይል ተዋጊ የአየር ምድቦች አንዱ በሆነው ምስራቅ አየር ምድብ ባለፍት 3 አመታት ተቋማዊ ሪፎርሙ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ” ሰራዊት ሀገር እንጂ ብሄር የለውም ” በሚል መሪ ቃል በተሰራው የሰራዊት ግንባታ ስራ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወገንተኝነት ፣ ከብሄርተኝነትና ከዘረኝነት አመለካከት በፀዳ መልኩ ተልእኮውን በላቀ ጀግንነት የሚፈፅም ጠንካራ ሰራዊት ከመገንባት አንፃር ሰፋፊ ስራዎች በመስራት አበረታች ውጤት መገኘቱን በኢ.ፌ.ድ.ሪ አየር ሀይል የምስራቅ አየር ምድብ አዛዥ የሆኑት ኮረኔል አበበ ለገሰ ተናግረዋል ።
በፕሮግራሙ ላይም የኢ.ፌ.ድ.ሪ አየር ሀይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ፣ ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች ፣ በኢ.ፌ.ድ.ሪ አየር ሀይል የምስራቅ አየር ምድብ አመራርና አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።


