በ 1962 ዓ.ም የተመሰረተው የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድ በወቅቱ ክቡር ዶክተር አሊ ቢራ ፣ አሊ ሸቦ ፣ ሀሎ ዳዌ እንዲሁም አልማዝ ተፈራና ሌሎችም የባንዱ መስራችና አባል በመሆን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተለያዩ ጣእም ያላቸውና በሀገራችን ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፍ የኦሮምኛና የተለያዩ ቋንቋ ያላቸውን ሙዚቃዎች ሰርተው ማበርከት ችለዋል ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በተለይም የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድ በኦሮሞ ባህልና ቋንቋ ላይ የፈጠረው አስተዋፆ እንዲሁም ደግሞ በኢኮኖሚው ፣ በፖለቲካውና በማህበራዊው መስክ ያበረከተውን አስተዋፆ የሚዳስስ የውይይት መድረክ የአፋን ኦሮሞ ዲፓርትመንት ከዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች በጋር በመተባበር በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል ።
በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድ መስራች የሆኑት ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ በርካታ አመታትን በማሳለፍ የራሱን አስተዋፆ መወጣት መቻሉን ተናግረው በቀጣይም የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የራሱን አስተዋፆ እንደሚወጣም የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ተናግሯል ።
የኦሮሞ ባህልና ሙዚቃ ላይ የተዘጋጀው ሴሚናር የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ቋንቋ ባህልና እሴት ብሎም ሌሎችን እሴቶችን በመጠበቅ ድሬዳዋ ከቱሪዝም የምታገኘው ገቢ ከፍ እንዲል ዩኒቨርሲቲው የራሱን አስተዋፆ ማበርከት እንዳለበት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም ተናግረው በቀጣይም የዩኒቨርሲቲው መምህራን በዘርፍ ላይ በትኩረት ሊሰሩበት እንደሚገባም ዶክተር ኡባህ ተናግረዋል ።
ሴሚናሮች አካዳሚያዊ ምርምሮች የሚቀርቡበትና እሱንም መሰረት በማድረግ ለምርምር መነሻ የሚሆኑ ሀሳቦች የሚገኙበት ብሎም የሰው ልጅን የእውቀት አድማስ ለማስፋት ከሚጠቅሙ መድረኮች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ተናግረው የአፋን ኦሮሞ ዲፓርትመንት ከዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ጋር በመተባበር በኦሮምኛ ቋንቋ ባህል ሙዚቃ ላይ ያተኮረ ሴሚናር በዩኒቨርሲቲው መካሄዱ በዘርፍ የተሰማሩ ምሁራን በመድረኩ ላይ ተሳታፊ እንደ መሆናቸው መጠን ስለ አፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድ ብሎም ስለ ኦሮሞ ባህልና ቋንቋን የተሻለ እውቀት እንደሚገኝበትም ዶክተር ሰለሞን ተናግረዋል ።
በፕሮግራሙ ላይም ዶክተር ገመቹ መገርሳን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ምሁራን እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በከተማው ላይ የሚገኙና 150 ለሚሆኑ ወጣቶች በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ስልጠና የሰጠ ሲሆን በቀጣይም መሰል ስልጠናዎችን ከመስጠት በዘለለ ተደራጅተው ፕሮፖዛል ነድፈው ለሚመጡ ወጣቶች ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደሚያደርግ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ተናግረዋል ።


