የአለም አቀፍ ደም ለጋሾች ቀንን ምክንያት በማድረግ በኮካ-ኮላ ፋብሪካ የደም ልገሳ ፕሮግራም ተካሂዷል ።

    ደም ከተለያዩ በጎ ፍቃደኛ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሰብስቦ አደጋ ለደረሰባቸው ፣ የደም ማነስ ላለባቸው ፣ በወሊድ ምክንያት ደም ለሚፈሳቸው ፣ የደም ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ህሙማን የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ደም ባንክ አገልግሎት ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን በ 2013 ዓ.ም 5 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብደብ አቅዶ 5 ሺህ 103 ዩኒት ደም መሰብሰብ ችሏል ።
    ከዚሁ ጋር ተያይዞም የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ደም ባንክ አገልግሎት በከተማው በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፍቃደኛ ከሆኑ ደም ለጋሾች ደም እየሰበሰበ የሚገኝ ሲሆን በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኘው የኮካ-ኮላ ፋብሪካም የአለም አቀፍ ደም ለጋሾች ቀንን ምክንያት በማድረግ የደም ልገሳ ፕሮግራም ተካሂዷል ።
    በኮካ-ኮላ ፋብሪካ ውስጥ በተካሄደው የደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ\ሮ ለምለም በዛብህ በድሬዳዋ አስተዳደር ከበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ደም በመውሰድ ህይወታቸው ሊያልፍ ለነበሩ እናቶች ህፃናት ብሎም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብተው የነበሩ ወገኖቻችንን ማትረፍ እንደተቻለና ይሄም ስራ አሁን ላይ በስፋት ተጠናክሮ መሰራት እንዳለበትና የሁሉንም ማህበረሰብ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ወ\ሮ ለምለም ተናግረው አስተዳደሩም የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ደም ባንክ አገልግሎት ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞችም ሆነ ባለሞያዎች የተለያዩ ወጪዎችን በመሸፈን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ከስጦታዎች ሁሉ ውድ ስጦታ የሆነውን ደም ነዋሪው ህብረተሰብ መለገስ እንዳለበትም ነው ወ\ሮ ለምለም የተናገሩት ።
    የአለም አቀፍ ደም ለጋሾች ቀንን ምክንያት በማድረግ በኮካ-ኮላ ፋብሪካ በተካሄደው የደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ የነበሩ የፋብሪካው ሰራተኞች በበኩላቸው በተለያዩ ጊዜያት የሚለገሰው ደም በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸው ሊያልፍ የሚችሉ እንዲሁም የደም እጥረት ላለባቸው ዜጎች ስለሚሆን ደም በመለገሳቸው መደሰታቸውን ተናግረው በቀጣይም የደም ልገሳውን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም ተናግረዋል ።