ለበርካታ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች የስራ እድል የፈጠረውን የራይት የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎንን የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጎብኝተውታል ።

    እ.ኢ.አ በ 1991 ዓ.ም በአንድ ደንበርካ ፣ በሁለት ሰከንድ አንድ ማሽን ፣ የጫት ሽርጥና አሮጌ ቴፕ በመያዝ ስራውን ” ሀ ” ብሎ የጀመረው የራይት የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን ባለቤት አቶ መዝገቡ ልኡለቃል ወይም በቅጥል ስሙ አብዛኛው የከተማችን ነዋሪዎች የሚያውቁት ኑኑሼ በርካታ የኑሮ ውጣ ውረዶችን በማሳለፍ አሁን ላይ በከተማችን ድሬዳዋ በግንባር ቀደምትነት የሚጠራ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን ባለቤት ከመሆኑም በዘለለ 106 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ እድል መፍጠር ችሏል ። የአቶ መዝገቡ ልኡለቃል ወይም ኑኑሼን የስራ ጥረት ከግምት ውስጥ ያስገባው የድሬዳዋ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የተመራ ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች የውበት ሳሎኑ ድረስ በመሄድ ጉብኝት አድርገዋል ።
    በተለይም አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛ የሆነ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ የተናገረው የራይት የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን ባለቤት የሆነው አቶ መዝገቡ ልኡለቃል ወይም ኑኑሼ ተናግሮ አሁን ላይ የተሻለ የውበት ሳሎንን ከፍቶ ከመስራቱም ባለፈ ለበርካታ የከተማው ነዋሪዎች የስራ እድልን እንደፈጠረና በቀጣይም ደግሞ በከተማው ትልቅ ማሰልጠኛ ተቋም በመስራት ለበርካታ የከተማው ነዋሪ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ማሰቡንና ለነዚህ እቅዶቼ መሳካትም አስተዳደሩ ድጋፍ ሊያደርግለት እንደሚገባም ተናግሯል ።
    በጉብኝቱ ላይም የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር የራይት የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን ባለቤት የሆነው አቶ መዝገቡ ልኡለቃል ወይም ኑኑሼ በከተማው ላይ ሶስት ቅርንጫፍ ያለውን የውበት ሳሎን በመክፈት በተለይም ለበርካታ የከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ የሆነ የስራ እድልን በመፍጠሩ ሊመሰገን እንደሚገባው ተናግረው አሁን ላይ እየሰራቸው ካላቸው ስራዎች በተጨማሪም በቀጣይ ለመስራት ያሰባቸው ስራዎች ይሳኩ ዘንድ አስተዳደሩ በቀጣይ ድጋፍ እንደሚያደርግለት አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
    በራይት የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ውስጥ አንዱ የሆነውና በወንዶች የውበት ሳሎን ላለፍት 18 አመት በመስራት ላይ የሚገኘው አ\ቶ ሰለሞን ይመር በውበት ሳሎኑ በመስራቱ በኑሮው ላይ የተሻለ ለውጥ ከማምጣቱም ባለፈ ለውበት ሳሎኑ ማደግ የራሱን አስተዋፆ ማበርከቱን ተናግሮ ሌሌችም የከተማው ነዋሪዎች በተሰማሩበት የስራ መስክ ጠንክረው በመስራት የተሻለ ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ አቶ ሰለሞን ተናግሯል ።
    እንደ አቶ ሰለሞን ይመር ሁሉ ላለፍት አምስት አመት በራይት የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን በማገልገል ላይ የምትገኘው ወ\ሮ መሰረት ዘውዱ አሁን ላይ የውበት ሳሎኑ ማናጀር ስትሆን በውበት ሳሎኑ ላይ በመስራቷ በስራዋ ብሎም በኑሮዋ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆነች ተናግራ ሁሉም የውበት ሳሎኑ ሰራተኞች እንደ ተቀጣሪ ሳይሆን በባለቤትነት ስሜት በመስራት ነገ ላይ የውበት ሳሎኑ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙና ማንኛውም ሰው ስራውን ሳይንቁ ባሉበት የስራ መስክ ጠንክረው በመስራት የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችሉም ወ\ሮ መሰረት ዘውዱ ተናግራለች ።