የተለያዩ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ የልማት ዘርፎችና ፕሮጀክቶች ውጤታማ የሚሆኑት በተጠናከረ የህብረተሰብ ተሳትፎ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በየአካካባቢው ለሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬታማነት የህብረተሰብ ተሳትፎን ማረጋገጥ የሚቻለው በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የልማት ጥያቄ መነሻ ያደረጉ የአካባቢ ልማቶችን በመለየት ቅደም ተከተል በመስጠትና የህብረተሰቡን የገንዘብ ፣ የቁሳቁስና የጉልበት አስተዋፆ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ነው ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በህብረተሰቡና በመንግስት የጋራ ተሳትፎ የተሰሩና ከ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወቶባቸው ተገንብተው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የምርቃትና የጉብኝት መርሀ-ግብር የተካሄደ ሲሆን እነዚህም ነምበርዋን ፣ ዲፖ ገንድ ሮቃ አካባቢ እንዲሁም መልካ ናቸው።
በ 03 ቀበሌ በተካሄደው የውስጥ ለውስጥ ኮብልስቶንና የጎርፍ መውረጃ ዲች ምርቃትና ጉብኝት መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ በተለይም ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን የውስጥ ለውስጥ የኮብልስቶን መንገድ በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች እንደሚሰራና ለነዚህም ስራዎች አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ አህመድ ተናግረዋል ።
አስተዳደሩ ከሚሰራቸው የልማት ስራዎች ጎን ለጎን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሰሩ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን የባለቤትነትና የኔነት ስሜትን የሚያሳድግ ከመሆኑም ባለፈ የድሬዳዋ አስተዳደር እንደ አስተዳደር ለህብረተሰቡ የሚጠቅሙ የልማት ስራዎችን በመስራት የህብረተሰቡን ችግር ከመፍታት አኳያም የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማለም የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም ተናግረዋል ።
በህብረተሰቡና በመንግስት የጋራ ስራ 4 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የውስጥ ለውስጥ የኮብልስቶን መንገድ ግንባታ ፣ የጎርፍ መውረጃ ዲች ፣ የውሀ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የከተማዋ ቀበሌዎች መገንባታቸውን የህብረተሰብ ተሳትፎና ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጎንፋ ሞሲሳ ተናግረው በቀጣይም ህብረተሰቡ ለመሰል ፕሮጀክቶች መሳካት ተሳትፎውን ከማድረግ ባለፈ አሁን ላይ የተሰሩትንም የልማት ፕሮጀክቶች በባለቤትነት ስሜት መጠበቅ እንደሚገባም አቶ ጎንፋ ሞሲሳ ተናግረዋል ።
ከዚህ ቀደም አካባቢያቸው ለጎርፍ ተጋላጭ ከመሆኑም በዘለለ ከፍተኛ የሆነ ቆሻሻ እንደነበርና አሁን ላይ ግን በህብረተሰቡና በመንግስት የጋራ ስራ አካባቢያቸው ከመፅዳቱም ባለፈ ከዚህ ቀድመ ያጋጥማቸው የነበረው የጎርፍ ችግር እንደቀለለና በዚህም መደሰታቸውን በ 03 ቀበሌ የልማት ፕሮጀክት ስራዎች የምረቃት ስነ-ስርአት ላይ ተሳታፊ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ።


