የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሃርላ የተሰኘ የምርምር ጽሁፎች ማቅረቢያ መጽሔት (journal) አስመረቀ፡፡
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግት ምክትል ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት የተዘጋጀውና ከድሬዳዋ ከተማ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጥንታዊዋ የሃራላ ከተማ ስም የተሰየመው የምርምር ጽሁፎች ማቅረቢያ መጽሔት (journal) በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተመርቋል ።
በዚሁም የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ኡባህ አደም ከዚህ ቀደም የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የምርምር ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት የምርምር ጽሁፎች ማቅረቢያ መጽሔት (journal ) ለማግኘት ብዙ ውጣ-ውረዶች ይገጥማቸው የነበረ መሆኑን አውስተው ሃርላ መጽሔት ለምርቃት መብቃቷ ግን የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ስራዎቻቸው ለህትመት እንዲበቃ ከማስቻሉም ባሻገር ሌሎች ወጣትና ታዋቂ ምሁራኖችም ሳይቀሩ ስራዎቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ኡባህ አክለውም ሃርላ የምርምር ጽሁፎች ማቅረቢያ መጽሔት በምሁራን መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲኖር ትልቅ አስተዋፆኦ እንደሚኖረውና የምርምር ጽሁፎች ማቅረቢያ መጽሔቱ (journal) በመላው አለም ታዋቂ በመሆን ዘላቂነት እንዲኖረው በዩኒቨርሲቲውና በየኮሌጆቹ የሚገኙት ምሁራንም የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም በእለቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለማህበረሰቡ ችግር የሚፈቱ ፣ እውቀትን የሚያሰድጉና አለማችን ለሰው ልጆች የተሻለችና ምቹ እንድትሆን ከማድረግ አንፃር ያላቸው ፋይዳ የማይተካ በመሆኑ እነዚህ የምርምር ውጤቶች ይሄን የማይተካ ሚናቸውን ለመወጣት እንዲችሉም ለህትመት በቅተው ለአንባቢና ለመላው ህዝቡ ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ተናግረው ይህንንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት የምርምር ጽሁፎች ማቅረቢያ መጽሔት (journal) ለምረቃ መብቃቱንም ዶክተር ሰለሞን ይፋ አድርገዋል፡፡
ለበርካታ ጊዜያቶች ተሞክሮ ስኬታማ ሊሆን ያልቻለው የምርምር ጽሁፎች ማቅረቢያ መጽሔት (journal ) መቋቋም እውን እንዲሆን ላበቁት የኮሚቴ አባላትና በስራው ላይ የተሳተፉ በሙሉ ትልቅ ምስጋና እንደሚገባቸው በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት ዶክተር መገርሳ ቃሲም ተናግረው በቀጣይነትም ውጤታማነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉንም ጥረት እንደሚጠይቅና ለዚህም መሳካት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚኖርበትም ዶክተር መገርሳ ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይም ለዚህ ስራ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፆኦ ላደረጉ የኮሚቴ አባለትና ምሁራን እንዲሁም ከመፅሔቱ ጋር ተያይዞ ሃርላ የተሰኘ ድህረ-ገፅ እንዲከፈት ላደረጉ ባለሙያዎች የእውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ተበርክቶላቸዋል፡፡


