የህዝቡን ውሳኔ በፀጋ በመቀበል ለተግባራዊነቱም እንደሚተጉ በድሬዳዋ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ:

    የድሬዳዋ አስተዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የ2013 ዓ.ም 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል::
    ምክር ቤቱ በመግለጫው በዘንድሮው ምርጫ ላይ የተለያዩ አካላት አሉታዊ ተፅእኖ ለማሳደር ጥረት ቢያደርጉም የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪ ተፅእኖውን ተቋቁሞ ሰላማዊ ምርጫ ማድረግ በመቻሉ የተሰማውን ደስታ ገልጿል::
    በአስተዳደሩ በምርጫው የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከ ድምፅ መስጫው እለት ድረስ ለነበራቸው ሰላማዊ ተሳትፎ የጋራ ምክር ቤቱ ምስጋና አቅርቧል::
    በተጨማሪም የድሬዳዋ አስተዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከዚህ በታች የቀረበውን ባለ6 አንቀፅ የአቋም መግለጫ አውጥቷል::
    1ኛ:- 6ኛው አገራዊ ምርጫ በከተማ አስተዳደራችን በሰላማዊ ሁኔታ አንድም ኮሽታ ሳይሰማ በመጠናቀቁ እኛ በድሬዳዋ ከተማ የምንገኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ እንገልፃለን::
    2ኛ:- በተለይም ሰላም ወዳዱ የድሬዳዋ ህዝብ ከሚነገርበት በተቃራኒው ሆኖ ከሌሊቱ 12:00 እስከ ምሽቱ 3:00 በአስተዋይነት ለሚፈልገው ፓርቲ ድምፁን በሰላም ለመስጠት ላሳየው ፅናት ሁሉም ፓርቲዎች ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን::
    3ኛ:- በድሬደዋ አስተዳደር የሚገኙ ሁሉም የፀጥታ ሀይሎች የምርጫ ሂደቱ ያለምንም እንከን እንከን እንዲከናወን ላደረጋችሁት ከፍተኛ ጥረት እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች እውቅና እንሰጣለን::
    4ኛ:- እኛ በከተማዋ የምንንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝቡን ውሳኔ በፀጋ በመቀበል ለተግባራዊነቱ እንተጋለን::
    5ኛ:- የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለምርጫው ስኬታማነት ላደረገው ጥረትና የምርጫ ቦታ እንዲሁም ቁሳቁሱ ምችችት ምስጋና እናቀርባለን::
    6ኛ:- በቀጣይም የድሬዳዋ ሰላምና ልማት ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ጋር ተቀናጅተን ለመስራት ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን::
    የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
    ሰኔ 22/2013 ዓ.ም
    ድሬዳዋ