የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በከተማችን ድሬዳዋ በሚገኙ የከተማም ሆነ የገጠር ቀበሌዎች ላይ ሰላማዊ የሆነ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ይኖር ዘንድ እንዲሁም በሁሉም አካባቢዎች የሰላም ፣ የፀጥታና የህግ-የበላይነት ይከበር ዘንድ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ። ፖሊስ ኮሚሽኑ እያከናውናቸው ከሚገኘው ሰላምና ፀጥታን ከማስጠበቅ እንዲሁም የህግ-የበላይነት ከማረጋገጥ በዘለለ በተለያዩ የስራና የግዳጅ አጋጣሚዎች ህይወታቸው ላለፍና ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊቱ አባላትና ቤተሰብ ድጋፍ እያደረገም ይገኛል ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው 6 ተኛው ዙር ምርጫ ላይ በድሬዳዋ አስተዳደር በስራ ግዳጅ ላይ በነበረበት ወቅት በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቱ ላለፈው ሳጅን እዩኤል ሀይሉ ቤተሰብ 200 መቶ ሺህ ብር እንዲሁም በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በስራ ግዳጅ ላይ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ህይወቱ ላለፈው ኮንስታብል ሳሙኤል ከተማ ቤተሰቦች የ 200 ሺህ ብር ድጋፍ ከመደረጉም ባለፈ በስራ ላይ ሆነው ህይወታቸው ላለፈው ረዳት ሳጅን ነስረዲን ጀማልና ለኮንስትባል ረመዳን አብዲ ለእያንዳንዳቻው የ 100 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጓል እንዲሁም በተለያዩ የፖሊስ ግዳጆች ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው የኮሚሽኑ አባላትም ለእያንዳንዳቸው የ 15 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍም ተደርጓል ።
በዚሁም የድጋፍ ስነ-ስርአት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ በተለይም ለአንድ ሀገር ሰላም መረጋገጥ ፖሊስ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለውና ለነዚህ ሁሉ ሀላፊነቶችም ከምንም በላይ የፖሊስ ሀይልን ከማጠናከር አንስቶ የተጎዱ የፖሊስ አባል ቤተሰቦችን ማገዝ እንደሚገባ ተናግረው ፖሊስ ኮሚሽኑን በሰው ሀይል ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ጭምርም በሚገባ ማደራጀት እንደሚገባም አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ተናግረዋል ።
በተለይም የፖሊስ ሰራዊት አባል ከየትኛውም ፓርቲና ፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ ሆነው የህግ የበላይነት እንዲከበር ከማድረግ አኳያ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩና እነዚህም ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አስተዳደሩም ከፖሊስ ኮሚሽኑ ጎን በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር ተናግረው በፖሊስ ግዳጅ ላይ ሆነው ህይወታቸው ላለፍ አባላት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀው የፖሊስ ኮሚሽኑ አባላትም በጀግንነት ስሜት ሀገሩንና ወገኑን ማገልገል እንደሚገባም አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አባላትና አመራሮች የሀገርን ሰላም ለማስከበር ህዝቦቿም ሰላም እንዲሆኑ በመደበኛውና በተለያዩ ግዳጆች ላይ በጀግንነት አካላቸውንና ህይወታቸውን ላጡ ፣ በግዳጅ አፈፃፀምና ፈታኝ በሆነው ህይወት በከፈሉበት ወቅት ሌላ ህይወት እንዳይከፈል ግዳጅ የተወጡ አባላቶችን በማመስገን ህይወታቸው ያለፈው አባላቶችን ለመዘከርና ታሪካቸውም በድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥም ህያው ሆኖ ለዘላለም የሚታወስ መሆኑን በማስመር እንደዚህ አይነት ነገሮችም በቀጣይ የሚወደሱ እንጂ ወደኋላ የማይመለሱ መሆኑን የመሰረት ድንጋይ የሚጣልበት ቀን መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረዋል ።
በፖሊስ ኮሚሽኑ ቅጥር ግቢው ውስጥ በተካሄደው በስራ ግዳጅ ላይ ሆነው ህይወታቸው ላለፈና ጉዳት ለደረሰባቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አባላትና ለአባላቱ ወላጆች ድጋፍ የማድረግ መርሀ-ግብር ላይም ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ፣ የፖሊስ ኮሚሽኑ አባላትና አመራሮች እንዲሁም የፖሊስ ኮሚሽኑ አባላት ወላጆች ተሳታፊ ሆነዋል ።


