የድሬዳዋ ወጣት ማህበር አደረጃጀት ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ ።
የድሬዳዋ ወጣት ማህበር ቀደም ሲል በድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ እ.ኢ.አ. በ 1996 አ.ም ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት ያገኘ የወጣት አደረጃጀት ቢሆንም ባለፍት አመታት በመዳከሙና በማዕከል ብሎም በቀበሌና በገጠር ክላስተር ደረጃ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለመሆኑ ምክንያት ማህበሩን በአዳዲስ አመራሮችና አባላት ማጠናከር በማስፈለጉ ምክንያት በዘጠኙም የከተማ ቀበሌዎችና በ 38 የገጠር ክላስተር ቀበሌዎች ከወጣቶች ማስተባበሪያ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በጋራ በመሆን የወጣት ማህበሩን የማደራጀት ፣ አመራሮቹን የማስመረጥና የአደረጃጀቶቹን ዝርዝር መረጃዎች የማደራጀት ስራዎች ተሰርተዋል ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የድሬዳዋ ወጣት ማህበር አደረጃጀት ጠቅላላ ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን በዚሁ ጉባኤ ላይም የድሬዳዋ ወጣት ማህበርን በከተማ አስተዳደር ደረጃ በማዋቀር ከከተማና ከገጠር ቀበሌዎች የተወከሉ ወጣቶች ያለማንም ጣልቃ ገብነት በዲሞክራሲ መንገድ ለቀጣይ ማህበሩን የሚመሩትን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሊቀመንበር ፣ ምክትል-ሊቀመንበር ፣ ዋና ፀሀፊ ፣ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሀላፊ ፣ የማደራጀትና ቅስቀሳ ዘርፍ ሀላፊ ፣ የማህበራዊ ዘርፍ ሀላፊና የትምህርት ተቋማት አደረጃጀት ሀላፊ በማህበሩ ደንብ መተዳደሪያ መሰረት ይመረጣሉ ።
በዚሁም ፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ከድር ጁሀር የድሬዳዋ ወጣቶች ማህበር ከቀበሌ እስከ አስተዳደር ድረስ ማህበሩን በማጠናከርና ወጣቶችን በማደራጀት አስተዳደራችንና ሀገራችን የሚጠብቁትን ጉልህ ድርሻ እንዲወጡና በተደራጀ አኳኋን ችግሮች እንዲፈቱ ለማስቻል የተሻለ የአደረጃጀት ቁመና ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት ተናግረዋል ።
አቶ ከድር ጁሀር አክለውም ማህበሩ የተቋቋመበት አላማና ተልዕኮ ለማሳካት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስከበር አመራር አባላቱ የሚጠበቅባቸውን ተግባርና ሀላፊነት በተሟላ ሁኔታ የመወጣትና በአስተዳደሩ እየተካሄደ ባለው ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴ ውስጥ ማህበሩ የላቀ ሚና በማበርከት በወጣቶችና በመንግስት መካከል እንደ ድልድይ በመሆን ለአስተዳደራችን ልማትና ብልፅግና የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በማጎልበት ረገድ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት በላቀ ትጋትና በቁርጠኝነት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ነው አቶ ከድር ጁሀር ያሳሰቡት ።
ከወጣት አደረጃጀት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት የአንድ ተቋም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች እገዛና ቅንጅታዊ አሰራር አስፈላጊ እንደሆነ የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ተናግረው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለማስወገድም የሴክተር መንግስት ተቋማት ፣ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም በዋነኝነት የወጣቶችን ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን አቶ ሻኪር አህመድ ተናግረዋል ።
በፕሮግራሙ ላይም የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ምክትል ሀላፊና የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ኡስማን አህመድን ጨምሮ የወጣት አደረጃጀት አመራሮችና አባላት ፣ የቀበሌ አመራሮች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።


