በዛሬው እለትም በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ የተለያዩ የከተማ ቀበሌዎች ውይይት ተካሂዷል።
የድሬዳዋ አስተዳደር በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ፣ ሀይማኖቶች በጋራ ፣ በፍቅርና በአንድነት ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ስትሆን የከተማዋ ነዋሪዎችም በተለያዩ ጊዜያቶች በሀገራችን ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ከመንግስት ጋር በመወያየት ከመፍታት ባለፈ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ዙሪያም ቢሆን በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይቷል ።
አሁን ላይም በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታና መንግስት የደረሰበት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን በተመለከተ እንዲሁም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በከተማው በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ላይ ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል ።
በትግራይ ክልል መንግስት የወሰነው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እንዲሁም በህዝቡ ውስጥ ያሉ እና የተፈጠሩ የሀሰት መረጃዎችን ግልፅ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በዛሬው እለት በየቀበሌዎቹ በተደረጉት ውይይቶች ላይ የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተዋል። ከዚህ ባለፈም ታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጲያዊያን በአንድነትና በተባበረ ክንድ እየገነቡት የሚገኘው ግድብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሀገራችን ህዝቦችም በአንድነት እና በጋራ በመተባበር የውጭ እና የውስጥ ጠላቶችን መከላከል እንደሚገባም በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
በውይይቱ ላይም ተሳታፊ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በሀገራችን ላይ በሚደረጉ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ላይ ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆን ለመስራት መዘጋጀታቸውንም በእለቱ ተናግረዋል ።


