በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የለሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች እያደረጉት ያለው የበጎ አድራጎት ስራዎች ለሌሎችም ክልሎች ምሳሌ እንደሚሆን ተገለፀ ።

    የለሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ከድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን የደም ልገሳ ፕሮግራም አካሂደዋል ።
    በድሬዳዋ አስተዳደር ከ 270 በላይ የሚሆኑ የለሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም የለሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች የድሬዳዋ አስተዳደር የለሊት ታክሲ የመረዳጃና የበጎ ፍቃድ ማህበር በሚል ስያሜ ለመቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎንም ማህበሩ እንደ ማህበር እስኪቋቋም ድረስ አባላቱ በከተማዋ ላይ የተለያዩ የበጎ-ፍቃድ ስራዎችን ለመስራት በእቅድ ደረጃ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ ። ለአብነትም የደም-ልገሳ ፣ የአረጋዊያንን ቤት ጥገና ፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ተማሪዎችን ለመደገፍ ይቻል ዘንድ 500 ደብተሮችን ማሰባሰብ ፣ የፅዳት ዘመቻ ፣ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብሮችን ለማከናወን በእቅድ ደረጃ በመያዝ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ።
    በዛሬው እለትም ” ነፍሱን ለሚሰጠኝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደሜን እለግሳለው ” በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የለሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች የደም ልገሳ ፕሮግራም አካሂደዋል። በዚሁም የደም ልገሳ መርሀ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ
    የለሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች እያደረጉት ያለው ስራ ለሌሎችም የኢትዮጲያ ከተሞችና ክልሎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ተግባር መሆኑን ተናግረው እነዚህንም ተግባራት በቀጣይም አጠናክረው ሊያስቀጥሉ እንደሚገባም ነው ኮሚሽነር አለሙ መግራ የተናገሩት ።
    የድሬዳዋ አስተዳደር የለሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች በከተማዋ ላይ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ለመስራት በእቅድ ደረጃ በመያዝ ወደ ስራ መግባታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር የለሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች የመረዳጃና የበጎ ፍቃድ ማህበር አባል የሆነው ወጣት ቃልኪዳን ፀሀዬ ተናግሮ በቀጣይም በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ላይ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በተጠናከረና በተቀናጀ መልኩ ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ነው ወጣት ቃልኪዳን ፀሀዬ የተናገረው ።