የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን በ 2013 በጀት አመት ከ 1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ ።
ግብር ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋፆ እንደሚኖረው ይታመናል ። የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣንም ከነዋሪውና ከንግዱ ማህበረሰብ ገቢን በመሰብሰብ ለከተማችን ድሬዳዋ ኢኮኖሚያዊ እድገት መሳካት ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ።
በዚህም መሰረት የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን በ 2013 በጀት አመት ከመንግስት ታክስና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ የመንግስት ታክስ በጠቅላላው 1 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 1 ቢሊዮን 658 ሚሊዮን 884 ሺህ 776.30 ብር መሰብሰብ መቻሉን የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዱሰላም መሀመድ ተናግረው ይህም አፈፃፀም በመቶኛ ሲቀመጥ 94.79 ፐርሰንት አፈፃፀም እንደተመዘገበና ይህም አፈፃፀም ከባለፈው በጀት አመት አንፃር ሲነፃፀር የ 22.48 ፐርሰንት ወይም የ 278 ሚሊዮን 250 ሺህ 082.92 ብር ብልጫ እንዳለውም ነው የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱሰላም መሀመድ የተናገሩት ።
በተለይም እንደ አስተዳደር ግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ለማበረታታት ይቻል ዘንድ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ምክንያት የተፈጠረውን ጫና ለመታደግ ይቻል ዘንድ 142 ሚሊዮን 826 ሺህ 695 ብር ምህረት ከመደረጉም በዘለለ ተቋሙን በቴክኖሎጂ በማዘመንና ግብር ከፋዩ ለህግ ተገዢ ይሆን ዘንድም ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ አብዱሰላም መሀመድ ተናግረው በ 2014 በጀት አመትም ያሉትን ጠንካራ ጎኖች በማስቀጠል የድሬዳዋን ተጨባጭ ሁኔታና የፌደራል እቅድን በመጠበቅ የተሻለ እቅድ በማቀድ የአስተዳደሩን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ነው የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዱሰላም መሀመድ ተናግረዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ከምን ጊዜውም በላይ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ይቻል ዘንድ ዝግጁ በመሆኑ ምክንያት ግብር ከፋዩ ማህበረሰብም በወቅቱ ግብራቸውን ሊከፍሉ እንደሚገባም ጥሪ ቀርቧል ።


