ለታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎቹ ተናገሩ ።

    የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ድሬዳዋ አስተዳደር ገብቷል ።
    ታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ የአሁኑን ትውልድ ከመጪው ትውልድ ጋር የሚያስተሳስር ኢትዮጲያዊያን አብረን በጋራ ማእድ መቋደስ ብቻ ሳይሆን በጋር መስራት እንደሚቻል ለአለም ያሳየንነት ህያው ምስክራችን ነው ። ታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ያለፍትን አምስት ወራት በሀረሪ ክልል ቆይታ አድርጎ ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር ሲገባ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችና የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ለግድቡ ዋንጫ ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል ።
    ታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ወደ ድሬዳዋ የገባበት ወቅት 2 ተኛው የግድባችን የውሀ ሙሌት እየተካሄደ ባለበትና አገራችን ኢትዮጲያ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ በፀጥታው ምክር ቤት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ድል በማስመዝገብ የህዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካዊያን እንዲታይ የተወሰነበት ወቅት ላይ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ተናግረዋል ።
    አቶ አህመድ አክለውም የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በድሬዳዋ በሚኖረው ቆይታ ሰፊ የሆኑ የህዝብ ተሳትፎና ንቅናቄ ስራዎችን በመስራት ለግድቡ ግንባታ የሚሆን በሚሊዮን የሚቆጠር የገቢ ማሰባሰብ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅም አቶ አህመድ ተናግረዋል ።
    የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ድሬዳዋ አስተዳደር ሲደርስ በህብረት በመውጣት አቀባበል ያደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በተለይም ዋንጫው ወደ ከተማችን ድሬዳዋ በመምጣቱ መደሰታቸውን ተናግረው በቀጣይም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት ።
    በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኘው ለገሀር አደባባይም ግድቡ የኔ ነው የሚል ቢልቦርድም ተመርቋል ።