በድሬዳዋ አስተዳደር የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጀመሯል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር በየአመቱ በሚካሄደው የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ በአስተዳደሩ በሚገኙ በከተማም ሆነ በገጠር የህብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱና ሊያግዙ የሚችሉ ዘርፈ-ብዙ የማህበራዊ አገልግሎት ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን በ 2013 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታን የመከላከል ፣ የችግኝ ተከላና ጥበቃ ፣ የደም ልገሳ ፣ የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት ፣ የመንገድ ደህንነት ፣ የአካባቢዎች ፅዳትና ውበት ስራዎች የሚሰሩ ይሆናል ።
ይኸውም የ 2013 የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች በድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመረ ሲሆን የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በይፋ ሲጀመርም 2 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን በከተማዋ ላይ የተዘጉ የጎርፍ መውረጃዎች ከማፅዳት ባለፈ የፊታችን ማክሰኞ ለሚከበረው የአረፋ በአል መስገጃ ሜዳንም በጋራ አፅድተዋል ፣ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር እንዲሁም ለመከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስና የአቅመ ደካሞችን ቤቶች የመጠገንና የማደስ ስራም ጀምረዋል ።
በዚሁም ፕሮግራም ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር ወጣቶቹ የጀመሩት የልማት ስራዎች የድሬዳዋን ማህበራዊ ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ የሚያቃልሉ እንደሆኑ ተናግረው ወጣቶቹ ያሰብትን እንዲያሳኩም አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አቶ ከድር ጁሀር የተናገሩት ።
በክረምት የበጎ አግልግሎት ተግባራት ላይ ከ 55 ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ከ 40 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የልማት ስራ አንደሚከወን የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ተናግረው በልማት ስራዎቹም በገጠርና በከተማ የሚኖሩ ከ180ሺ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተናግረዋል ።
በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ የተሳተፉት ወጣቶች በበኩላቸው የገጠርና የከተማ ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል የሚያከናውኑትን ተግባራት በተቀናጀ ቁርጠኝነት ዳር በማድረስ ድሬዳዋን በክረምቱ ወራት ፅዱና ውብ የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረው ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በጋራ መሰባሰባቸውም ህብረታቸውንና አንድነታቸውን አጠናከረው በህብረት ያላቸውን አንድ አገር ለማሻገር እንደሚያግዛቸውም ነው ወጣቶቹ የተናገሩት ።
የ 2013 የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ማስጀመሪያ ስነ-ስርአት ላይም የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋና የካቢኔ አባላት እንዲሁም ከተለያዩ የከተማዋ ቀበሌዎች የተውጣጡ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል ።


