የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ አበክረው መስራት እንደሚገባቸው ተገለፀ::

    የምስራቃዊ እድገት ፋና የነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ከyouth and cultural development foundation(YCDE) ጋር በመተባበር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስነ-ዜጋ ትምህርትን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ፡፡
    በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ የሀይማኖት አባቶችና የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች የሰላም ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት አይነት ቢካተት ወጣቱ በሰላም የመኖርና ልማት ላይ የመሳተፍ እንዲሁም የሰብአዊ መብትን ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ሲሉ የተናገሩት የYCDE ዳይሬክተር ዶ/ር ግርማ ምትኩ ናቸው፡፡
    ዶ/ር ግርማ ከዚህም ጋር አያይዘው ቀደም ሲል የነበሩንን ሀገር በቀል የሆኑ የግጭት አፈታትና የሰላም ማስፈኛ ባህሎችን በማስቀጠልምና በማዳበር እንደዚሁም ለወጣቱ ትውልድ በሚገባ በማስተማር ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን በማስቀረት ሰላምን ለማስፈን ያለው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
    ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተጨማሪም ቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ ሰላምን በጋራ በመጠበቅና ሰላምን ሊያውኩ የሚችሉ ጉዳዩችን ቀድሞ በመከላከል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ዶ/ር ግርማ ገልፀዋል፡፡
    በስልጠናው የተሳተፉ ተሳታፊዎችም እንደተናገሩት በተሰጠን ግንዛቤ መሰረት በትምህርት ካሪኩለሙ ቢካተት የሀገራችንን ሰላም አስጠብቆ ለመጓዝ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡