ለ2 ቀናት ሲካሄድ የቆየው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 2ኛ የስራ ዘመን 47ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አጀንዳዎችን በማፅደቅ ተጠናቋል።
የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት የ2013 ሪፖርትና የ2014 በጀት አመት እቅድ በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አስተባባሪ ኮሚቴ ታይቶ እንዲጸድቅ በሙሉ ድምጽ ምክር ቤቱ ውክልና ሰጥቷል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የ2013 ሪፖርትና የ2014 በጀት አመት እቅድ በምክር ቤቱ ጸሀፊ የተከበሩ አቶ ስንታየሁ ማሞ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ጸድቋል፡፡
የመሬት ምዝገባ ጽ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ በምክር ቤቱ የማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሰላማዊት አስፋው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ጸድቋል፡፡
የ2013 ተጨማሪ በጀት በድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ የተከበሩ አቶ ሱልጣን አሊዪ ቀርቦ ጸድቋል፡፡
በተመሳሳይም ድሬዳዋ አስተዳደር የ2014 አመት አጠቃላይ በጀት ብር 4,882,482,131 ሆኖ የቀረበ ሲሆን የምክር ቤቱ የበጀት ‘ኢኮኖሚ ‘ንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አይናለም ተዘራ የውሳኔ ሃሳብ እና በምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ተሰጥቶበት ጸድቋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 47ኛ መደበኛ ጉባኤ የመጨረሻ አጀንዳ የነበረው የሹመት ስነ-ስረአትም ተካሂዷል፡፡
በዚህም መሰረት በድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ አቅራቢነት አቶ ሰሚር ረሺድ የድሬዳዋ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን የተሾሙ ሲሆን የቃለ መሀላ ስነ-ስረአቱንም የድሬዳዋ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ አደን አስፈጽመው ጉባኤው ተጠናቋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላትም በነገው እለት በአስተዳደሩ 4ቱም ክላስተሮችና 9 የከተማ ቀበሌዎች በሚደረገው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በየአካባቢያቸው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት


