ሁለተኛው ዙር የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በማስመልከት በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት የፖናል ውይይት ተካሄዷል።
የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን ከሆነበት ጊዜ አንስቶ መላው የሀገራችን ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ ጉልበታቸውን ፣ እውቀታቸውን ፣ ሀብታቸውን ፣ ጊዜያቸውን መስዋት በማድረግና በጋራ በመቆም ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ ።
ከታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት ለአንድ ቀን የቆየ የፖናል ውይይት ተካሂዷል ። በዚሁም የፓናል ውይይት ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ኡባህ አደም ሀገራችን ኢትዮጲያ የአባይ ወንዝን ለመገደብ በተለያዩ መንግስቶቿ ሞክራ ሳይሳካላት መቅረቱን አስታወሰው ይህ ትውልድ ግን ወንዙን ለመገደብ በሚያደርገው ጥረት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ይቻል ዘንድ የፖናል የውይይት መድረክ ማዘጋጀት መቻሉን ዶክተር ኡባህ ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአይቻልም መንፈስን ከመስበሩም በዘለለ የግድቡ ግንባታ ከተወሰነበት ጊዜ አንስቶም በሀገር ውስጥና በተለያዩ የውጪ ሀገራት የሚገኙ መላው የሀገራችን ህዝቦች በገንዘብ ፣ በጉልበት እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክም ቢሆን ከፍተኛ አስተዋፆ ማበርከታቸውን የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ መሀመድ ቡህ ተናግረዋል ።
በታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ህብረተሰቡ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራ ማካሄድ እንደሚጠበቅበት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተናግረው የአባይ ውሃ መገኛ የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከወንዙ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ትሆን ዘንድም ተግተን መስራት እንደሚጠበቅብን ሚኒስቴር ዴታው በፓናል ውይይቱ ላይ ገልፀዋል።
ታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብን ተተርሶ በሀገራችን ላይ እየደረሰ ያለው ተፅእኖ ከግድቡ በላይ እንደሆነና ግድቡ የጥገኝነት ተፅእኖን ለመስበር ከአድዋ ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የቆሙበት መሆኑን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሌክተር የሆኑት ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናግረው ምእራባውያኑ ከግድቡ በዘለለ የኢትዮጵያውያን አንድ መሆን እንዳሳሰባቸውም ነው ዶክተር አረጋዊ በርሄ የተናገሩት ።
በዚሁ የፓናል ውይይት ላይም የአገራችን ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን ከፓናል ውይይቱ ጎን ለጎንም የደም ልገሳና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብርም ተካሂዷል ፡፡


