ድሬዳዋ ጀግኖቿን በክብር አመሰገነች ።

    ከተማችን ድሬዳዋ አንጋፋና ስመጥር የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት የቻለች ከተማ ነች ። ለአብነትም እነ ተካበ ዘውዴና ቢተው አብሬ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናቸው ። በተለይም ተካበ ዘውዴ በክለብ ደረጃ ድሬዳዋ ከተማና ድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ የተጫወተ ሲሆን በብሄራዊ ቡድንም ረጅም አመት በግብ ጠባቂነት ከመሰለፍ ባለፈ ሀገራችን ኢትዮጲያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫን ባሸነፈችበት ወቅት በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል አስተዋፆ በማበርከት የትውልድ ከተማው ድሬዳዋን ብሎም ሀገሩን ማስጠራት ችሏል ። ቢተው አብሬም በክለብ ደረጃ ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተ ሲሆን ለብሄራዊ ቡድንም በ 1980 ዎቹ በሴካፋ ውድድር ኬንያ ላይ በአጥቂነት መጫወት የቻለና እንደ ተካበ ዘውዴም ከተማውንና ሀገሩን ማስጠራት የቻለ ተጫዋች ነው ።
    የከተማችንን ብሎም የሀገራችንን ስም በጉልህ ማስጠራት የቻሉት ጀግኖቻችን አሁን ላይ ኑሯቸውን በአሜሪካን ሀገር ቢያደርጉም ነገር ግን የድሬዳዋ ተወላጃችና ወዳጆች ማህበርን በማቋቋም የኮቪድ 19 መመርመሪያ ማሽንን ለከተማዋ ገዝተው ከማስረከብ ጀምሮ ፣ አቅመ ደካሞችን መደገፍ ፣ ወላጅ አልባ ተማሪዎችን መደገፍ ብሎም በበርካታ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ ።
    ታዲያ ከተማችን ድሬዳዋም ለነዚህ አንጋፋና ስመጥር የሆኑ ልጆቿን የአስተዳደሩ ከንቲባን ጨምሮ ፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደምና ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ፣ ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች ፣ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ፣ ባለድርሻ አካላትና ነዋሪዎች በተገኙበት በክብር ከማመስገን ባለፈ እውቅናም ተሰቷቸዋል ።
    በዚህ የእውቅና መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ የድሬዳዋ ከተማ ከዚህ ቀደም በስፖርቱ መስክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደነበረችና አሁን ላይም በስፖርቱ መስክ የቀድሞ የከተማዋ ስም ለማስመለስ ነባር ስፖርተኞች የአሁኑን ትውልድ ስፖርተኞች በተለያዩ መስኮች ከማበረታታት አንስቶ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረው የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበርም ከአስተዳደሩ ጎን በመሆን እያደረጉት ላለው ድጋፍም ክቡር ከንቲባው ከልብ አመስግነዋል ።
    ድሬዳዋ ከዚህ ቀደም በነበረው የስፖርት ታሪኳ እጅግ ጥሩ ስም እንደነበራትና ነገር ግን አሁን ላይ በከተማዋ በስፖርቱ መስክ የሚታዩትን መቀዛቀዞች በጋራ በመሆንና በመስራት የቀድሞ ዝናዋን ማምጣት እንደሚገባ ተካበ ዘውዴ ተናግሮ በቀጣይም በሚችለው መጠን ለከተማው ስፖርት ማደግ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ተካበ ዘውዴ ተናግሯል ።
    በስፖርቱ መስክ የቀድሞ የከተማዋን ስም ለማስመለስ በተለይም የማዘውተሪያ ቦታዎች በከተማዋ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሊኖሩ እንደሚገባ ቢተው አብሬ ተናግሮ አስተዳደሩ ላደረገላቸው የምስጋናና የእውቅና ፕሮግራም ቢተው አብሬ ከልብ አመስግኗል ።