ኪነ – ጥበብ አገራዊ አንድነትን ለማጠናክር ያለው ሚና የጎላ መሆኑ ተገለፀ ::

    ኪነ – ጥበብ ለአገራዊ አንድነትን በሚል መሪቃል የሃገር መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለውን የህልውና ዘመቻ ለመደገፍ ያለመ መድረክ ተካሂዷል።
    በዝግጅቱ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሃመድ ቡህ ኪነ – ጥበብ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ፣ዜጎችን ለአንድ አላማ ለማሰለፍ ብሎም ሰላምን ለመስበክ የሚጫወተው ሚና የላቀ መሆኑን በተለያየ የታሪክ አጋጣሚዎች ተመልክተናል ብለዋል።
    በአገራችን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዜጎችን ከፋፍሎ አገርን ለማፍረስ ከውስጥም ከውጪም ሰላማችንን በማይፈልጉ ሃይሎች በርካታ ጥቃቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ በመሆኑም የነዚህን ሃሎች ሴራ መክቶ አንድነትን በማጠናከር ሰላማችንን ለማረጋገጥ የኪነ – ጥበብን እምቅ አቅም መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል።
    በመሆኑም ሁሉም ዘዜጋ እያሳየ ያለውን ለአገር ክብር ተቆርቋሪነት ስሜት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተሰጧቸውን በመጠቀም አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ፣ ዜጎችን ለአንድ አላማ ለማሰለፍ ብሎም ሰላምን በመስበክ ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለውን የህልውና ዘመቻ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
    በመድረኩ የተለያዩ የኪነ – ጥበብ ስራዎችን ካቀረቡ አርቲስቶች ያነጋገርናቸው ሃገር ከምንም ነገር በላይ ይቀድማል ኪነ -ጥበብ ሰው ፣ ኪነ -ጥበብ ሰላም ማለት ነው ። ሰው ከሌለ ስላም ከሌለ የኪነ-ጥበብ ዋጋዋ ያነሰ ነው ፣ በመሆኑም ማንኛውም የኪነ-ጥበብ ባለሙያ በሃገራዊ ስሜት በጋራ ለአንድነት መስራት ይገባል ብለዋል።በቀጣይም አገራቸው ለምትፈልገው ማንኛውም ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ አመላክተዋል።በመድረኩ የሃገር ፍቅርን የሚሰብኩ ግጥሞች ፣ መነባንብ፣ ድራማ እንዲሁም ፣ጥዑመ ዜማዎች እና መልዕክቶች በሰፊው ተላልፈዋል ።