ዛሬ በድሬዳዋ ምድር ባቡር ሜዳ በተከናወነው የስንቅ ማዘጋጀት መርሀግብር ላይ ከድሬዳዋ ሁሉም የከተማ ቀበሌዎች የመጡ ሴቶች የተሳተፉ ሲሆን መከላከያ ሰራዊታችን ድል እስኪጎናፀፍ ድረስ የደጀንነት ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቺያ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፋጡም ሙስጠፋ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት የድሬዳዋ እናቶች ሀገር ለማዳን እየተደረገ ባለዉ ዘመቻ ላይ ስንቅ በማዘጋጀት እያበረከቱ ለሚገኙት ከፍተኛ አስተዋፆ የሚያስመሰግን መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ከንቲባ አህመድ ቡህ በየቀበሌውና በየሰፈሩ ለመከላከያ ሠራዊት እየተካሄደ ላለው የስንቅ ዝግጅት ምስጋናና አድናቆታቸውን ገልፀው በግንባር ተሰልፎ ለአገሩ ክብር ህይወቱን ለመሰዋት ለሚሰለፈው ሰራዊት ስንቅ አዘጋጅቶ በመላክ የኢትዮጵያ ሴቶች የሚፈፅሙት የደጀንነት ሚና ከአደዋ ጀምሮ እስከ ቅርቡ የባድመ ጦርነት ድረስ ለተገኙት ታሪካዊ ድሎች በምንም የማይተካ የላቀ አስተዋጽኦ እንደነበረው ተናግረዋል።
መንግሥት ያቀረበውን የእናት አገር ጥሪ ተቀብላችሁ እያደረጋችሁት ያለውን የሚያኮራ እንቅስቃሴ አሸባሪው ሐይል ተደምስሶ ሞቱ በይፋ እስኪታወጅ ድረስ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉበት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። የድሬዳዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከድሬዳዋ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የስንቅ ድጋፍ በመርሀግብሩ ላይ ያስረከበ ሲሆን በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል። በዝግጅቱ ላይ አፈጉባኤ ፈጡም መሐመድ እና ምክትል ከንቲባ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የመንግሥትና የፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና በርካታ የከተማ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡


