አቶ ቴድሮስ ብርሃኑ ይባላል ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን በሹፍርና ሙያ ህይወቱን እየመራ ይገኛል። ቀደም ሲል የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን አገሩን አገልግሏል ። ከማንም ከምንም በላይ ሃገር ይቀድማል የሚለው አቶ ቴድሮስ የሹፍርና ሙያውን ትቶ፣ ቤተሰቦቹንም ተሰናብቶ አገራን ለማዳን እዘምታለው የትም መቼም በምንም በሚለው የዘመቻ ጥሪ ወደ ግንባር ለመሄድ ተዘጋጅቷል።
አገር ሰላም ካልሆነ ማንኛውም ዜጋ ሰላማዊ ሂወት መምራት አይችልም ልጆቼም ሆኑ ቤተሰቤ እንዲሁ ሰላም ማግኝት አይችሉም።ስለሆነም በቀድሞ የውትድርና ሙያዬ አገሬን ዳግም ለማገልገል የወሰንኩት የቤተሰቤን ሰላም ለማስጠበቅ ነው ሲል አቶ ቴድሮስ ሃሳቡን ይገልፃል።ባለቤቴ ወደ ግንባር እንዲሄድ ተመካክረን አምነንበት ነው የወሰነው ትላለች የአቶ ቴድሮስ ባለቤት።
አንደ አቶ ቴድሮስ ሁሉ በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ያገኝናቸው ዳግም ዘማቾች በተመሳሳይ የሃገርን ህልውና ለማስከበር የማይከፈል ዋጋ አይኖርም ህይወታችንን መስዋት አድርገን የአገራችንን ህልውና ከውጪም ከውስጥም ካሉ የሚቃጣውን ትንኮሳ ለመመከት ዝግጁ ነን ሲሉ አቛማቸውን አንፀባርቀዋል።
በሽኝት ስነስረአቱ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሃመድ ቡህ ካለማንም አስገዳጅነት በፍቃዳቹ የአገራችሁን ህልውና ለማስከበር ዳግም ለመዝመት መወስናቹ ለሃገራቹ ያላችሁን ፍቅር የሚያመላክትና ለሌሎች ተምሳሌት የሆነ የጀግንነት ውሳኔ ነው ሲሉ ተናግረዋል።የፈፀማችሁት ተግባር በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቅ የሚፃፍ በመሆኑ ልትኮሩ ይገባል ሲሉ ምክትል ከንቲባው ለዳግም ዘማቾቹ መልክት አስተላልፈዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ ጠሃ በበኩላቸው ከምንም ጊዜውም በላይ ሃገራችን የኛን የልጆቿን አንድነት የምትሻበት ወቅት አሁን እንደመሆኑ በፍቃዳቹ አገራችሁን ዳግም ለማገልገል መወሰናቹ የላቀ የጀግንነት ተግባር ነው ሲሉ ስሜታቸውን አንፀባርቀዋል።ሌሎቻችንም ቢሆን በጦር ግንባር ተሰልፎ የሃገርን ክብር ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በየተሰማራንበት ዘርፍ ለወገንና ለሃገር የሚጠቅም ስራ በመፈፀም ለኢትዮጵያችን ያለንን ፍቅር በተግባር ማሳየት ይገባል ብለዋል አቶ ሙሳ


