አሸባሪው የህውሀት ቡድን ሀገርን የማፈራረስና የመበታተን የሽብር ተግባርና ተልእኮ የማምከንና ህግን የማስከበር ሀገራዊ ጥሪን ተከትሎ የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የልዩ ሀይል አባላት ህግን በማስከበሩ ግዳጅ ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኙ መላው የከተማዋ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች በጋራ በመሆን በገንዘብ ፣ በጉልበት ፣ ስንቅ በማዘጋጀት ፣ የእርድ ከብት በመለገስ ብሎም የህግ-ማስከበር ግንባር ድረስ በመዝመት ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ በጉልህ ማሳየት ችለዋል ።
በዚህም መሰረት የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ለጀግናው የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ያደረጉትን የስንቅ ፣ የእርድ ከብት ፣ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ በአዲስ አበባ በሚገኘው የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ዋና መስሪያ ቤት የርክክብ ስነ-ስርአት ተካሂዷል ።
በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት አቶ አህመድ ሺዴ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ፣ ባለሀብቶች ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለመከላከያ ሰራዊት ያደረጉት ድጋፍ በተለይም የሀገራችንን ሰላምና ህልውና ለመጠበቅ ለሚደረገው ዘመቻ በእጅጉ የሚያበረታታ መሆኑን አቶ አህመድ ሺዴ ተናግረዋል ።
በገንዘብ ፣ በስንቅ ፣ በሞራል እንዲሁም በጉልበት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን የድሬዳዋ አስተዳደርና ነዋሪዎች ድጋፍ በማድረጋቸው በሀገር መከላከያ ሚኒስቴርና በጀግናው መከላከያ ሰራዊት ስም የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ወ\ሮ ማርታ ሉዊጂ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
ለጀግናው የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ፣ የሴት አደረጃጀት ፣ ወጣቶች ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ ባለሀብቶች ፣ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም የተለያዩ አካላት የ 28 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍና 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ደግሞ የአይነት ድጋፍ በአጠቃላይ 31 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረግ መቻሉን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ለኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በማድረጉ የዲሞክራሲ ማእከል ማስተባበሪያ ሚኒስቴር ድኤታ የሆኑት ዶክተር ተመስገን ፍርቃ ምስጋናቸውን በእለቱ አቅርበዋል ።
በፕሮግራሙ ላይም የፌደራል መንግስት ፣ የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊትና የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ፣ አባገዳዎች ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።


