የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ መሰጠት ጀምሯል። ከትግራይ ክልልና በወቅታዊ ጉዳዮች ተጽዕኖ ስር ከሌሉ አካባቢዎች በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ፈተናው እየተሰጠ ይገኛል።
በድሬዳዋ አስተዳደርም ዛሬ ማለዳ ፈተናው መሰጠት ጀምሯል። የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ም/ሀላፊ አቶ ሀለኔ ሀሰን እንደገለጹልን ብሔራዊ ፈተናው ያለችግር ይጠናቀቅ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ዝግጅት ተደርጓል።
አሁን ፈተናውን የሚወስዱት ተማሪዎች በ2013 ዓ.ም በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት የትምህርት መርሀግብሩ በመቀየሩ ምክንያት የማካካሻ ትምህርት ተሰጥቷቸው የተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀለኔ በድሬዳዋ አስተዳደር በጥቅሉ 2424 ያህል ተፈታኞች ለፈተናው መቀመጣቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 617 ሺህ ተፈታኞች ፈተናውን እየወሰዱ መሆኑም ታውቋል።


