ነዋሪው ህብረተሰብ ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በጋራ በመሆን የአሸባሪውን የህወሀት ቡድን ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባ ተገለፀ ።

    አሸባሪው የህወሀት ቡድንና የኦነግ ሸኔ ቡድን በተለይም በአፋር ፣ በአማራ ክልል እንዲሁም በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የፈፀሙትን ጥቃትና ወረራ በማክሸፍ ደረጃ ነዋሪው ህብረተሰብ ከዳር እስከ ዳር ተነቃንቆ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን ሴራ ለመቀልበስ ህዝባዊ ንቅናቄ ይፈጠር ዘንድ እንዲሁም የተጀመረው ትግል የህዝብ ትግል ሆኖ አሸባሪው የህወሀት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገድ ዘንድም የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ ።
    በድሬዳዋ አስተዳደርም ይሄኑኑ ወቅታዊ ጉዳይ ተከትሎ 6 የኮሚቴ መዋቅሮችን በማዋቀር ወደ ስራ የተገባ ሲሆን ይሄም መዋቅር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ የአስተዳደሩ የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ እዝ ተቋቁሞ በክቡር ከንቲባው የሚመራ ሆኖ ከፀጥታ አኳያ እንደ አስተዳደር ያሉ ስጋቶችን ቀድሞ በመተንተን አዋጁን የማስፈፀም ዋና ተልእኮ አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።
    አቶ እስቂያስ አክለውም ተከታታይ የሆኑ የህዝብ መድረኮችን በመፍጠር የመንግስት ሰራተኛ ፣ ነዋሪዎች ፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ፣ ወጣቶች እንዲሁም ሴቶችን ታሳቢ ያደረጉ የፖለቲካ ስራዎች ፣ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ብሎም የገፅ-ለገፅ የመድረክ ውይይት እንደሚካሄዱና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በይበልጥ በመስራት የህዝብ መነሳሳትን በመፍጠር ንቅናቄው በዋናነት በማህበረሰቡ ውስጥ ሙሉ እንዲሆን ከማድረግ አኳያና የተሰሩ ስራዎች ግልፅና ትክክለኛ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ የተሳሳቱ መረጃዎችን ደግሞ የማረም ስራዎች እንደሚሰራ አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።
    በፓርቲ ውስጥ ባሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የፀጥታና ፍትህ ቢሮ እንዲሁም ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ካሉ ተወካዮች ጋር የሚሰራ አዲስ የሀገር መከላከያ ስራዊት ምልመላን ታሳቢ ያደርገ የንቅንቄ ስራዎች እንደሚሰራና ከመከላከያ በተለያየ ምክንያት ተቀናሽ የሆኑ ሀይሎችና የቀድሞ ሰራዊት አባላትን መልሶ ጥሪ በማድረግና ለዘመቻው ዝግጁ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አቶ እስቂያስ ተናግረው የወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረጉ የመከካከያ ሰራዊት ድጋፍና መሰረታዊ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎችንም መሰረት በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን ክትትል በማድረግ ቶሎ ብሎ ወደ ስራ እንዲገቡ ከማድረግ አኳያና አጠቃላይ የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት ላይ ትኩረት ተደርጎ የንግድ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመሰራት ላይ እንደሚገኝም ተገልፃል ።
    በተለይም ነዋሪው ህብረተሰብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በጋራ በመሆን የጀመረውን መረጃ የመስጠትና በሁሉም አካባቢዎች በቅንጅት ፀጥታን የማስጠበቅ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ቀደም ሲል በተሰጡት የፖሊስ ስልክ አድራሻዎች መሰረት ፀጉሮ ልውጦችን ፣ በየአካባቢው የሚያጠራጥሩ ሁኔታዎች ሲያዩ በስልኮቹ አማካኝነትና ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በአካል በመቅረብ የአሸባሪውን የህወሀት ቡድን ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባም አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።