ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከስምንት መቶ ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ላደረጉ የሸማቾችና የየህብረት ስራ ዩኒየኖች ዕውቅና ተሰጠ

    ሸማቾችና ዩኒየኖችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ፡፡
    በእውቅናና ምስጋና ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሀር የሸማቾችና የየህብረት ስራ ዩኒየኖች የሀገር መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ላለው ኢትዮጵያን የማዳንና ትውልድን የማስቀጠል የህልውና ዘመቻ ላበረከታችሁት ድጋፍ ከልብ አመሰገናለሁ ብለዋል ፡፡
    ከንቲባ ከዲር ጁሀር ሀገርን የማዳን ዘመቻው በአስተዳደረችን ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ ፣ ጉልበት ያው በጉልበቱ በመሰለፍ ከሀገር መከላከያ ጎን የመሰለፍ ግዴታ አለብን ብለዋል ፡፡ የተደረገው ድጋፍ በገንዘብና በዓይነት ከስምንት መቶ ሺህ ብር በላይ ሲሆን ይህም ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል ፡፡
    ከንቲባው በመዝጊያ ንግግራቸው የህዝባችንን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ የተጀመረው የቅዳሜ ገበያ በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይወሰን ቦታዎችን በመቀያየር ሁሉንም አካባቢ ተደራሽ እንዲያደርግ እያሳሰብኩ አስተዳደሩ ስራችሁ የተሳካ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ይወጣል ብለዋል ፡፡
    ድጋፉን የተረከቡት የምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል አዛዥ ኮሌኔል ብርሃኑ ዘውዱ የተደራጀ ኃይል ያሸንፋልና እናንተም በማህበር ተደራጅታችሁ ለሀገራችሁ ያላችሁን ፍቅርና ክብር የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በገንዘብና በቁሳቁስ መደገፋችሁ ኢትዮጵያዊነታችሁን የሚገልጽ በመሆኑ ልትኮሩ ይገባችኋል ብለዋል ፡፡ እዚህ እናንተ የምታደርጉት ድጋፍ ጁንታው ላይ የሚያርፈው በትር ጠንከር እንዲል ያደርገዋልና ድጋፋችሁ ተጠናክሮ ይቀጥል ሲሉ አሳስበዋል ፡፡ ፡፡