የኢፌድሪ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ፈይሳ ሹርኬ የድሬዳዋ ህዝብ ሀገር በህልውና ማስከበር ጦርነት ውስጥ እንደሆነች አውቆ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያከበር ፤ የመንግስት ሰራተኛውም ከሌላው ጊዜ በተለየ የኃላፊነት ስሜት ህዝብ እንዲያገለግል ጥሪ አቀረቡ ፡፡
ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አሁን ያለንበትን ሁኔታ በመደበኛ የህግ አካሄድ ካለንበት ሁኔታ መውጣት የማያስችለን በመሆኑ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ዕድሜያቸው የሚፈቅድላቸው ወጣቶች የሀገር መከላከያን ተቀላቅለው ስልጠና እንዲዋስዱና የሽብር ኃይሉን እንዲመክቱ ፣ ጦር ሜዳ መሄድ የማይችሉና የጦር መሳርያ በእጃቸው የሚገኝ ሰዎች መሳርያዎቻቸውን ለጸጥታ ክፍሉ እንዲያስረክቡ ፤ የጸጥታ ኃይሉ ምክኒያታዊ ጥርጣሬ አድሮበት ለሚያደርጋቸው ማንኛውም ኦፐሬሽን ሁሉም ዜጋ ትብብር ማድረግ ይገባዋል ብለዋል ፡፡
ሆን ብሎ የሚከወን የኢኮኖሚ አሻጥር ለመፍጠር ምርትን የሚደብቁም ሆነ ምርት ከማምረት የሚያስተጓጉሉ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች በዕቅድ የሚመራ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው ያስታወቁት ኃላፊው በተመሳሳይ ሽብርተኞችን በስነ – ልቦና ሆነ በኢኮኖሚ ለመደገፍ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚደረግ እንቅስቃሴ በአዋጁ ክልከላ ተጥሎበታል ብለዋል ፡፡
ጠቅላይ ዐቃቢ ህጉ የመረጃ ስርጭትን በሚመለከት ፡- በማህበራዊ ትስስር ገጾችም ሆነ በመደበኛ ብዙሃን መገኛኛዎች ሽብርተኞችን የሚደግፍ መልዕክትም ሆነ የተዛባ መረጃ ማሰረጨት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚያስቀጣ በመሆኑ መረጃ ከመሰራጨቱ በፊት አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል ፡፡
ጠቅላይ ዐቃቢ ህጉ የጸጥታ ኃይሉ ላይ የተጣለውን ገደብ በሚመለከት ምክኒያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል ዕርምጃዎችን መውሰድ በአስቸኳይ አዋጁ የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል::


