በሀገራችንም ብሎም በድሬዳዋ አስተዳደር የኮቪድ-19 ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ ከመጋቢት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በመላው ሀገራችን ላይ መሰጠት ቢጀምርም ክትባቱን እየወሰዱ ያሉ ሰዎች ቁጥር ግን በተፈለገውና የወረርሽኙን ስርጭት መቆጣጠር በሚያስችል መልኩ ባለመሆኑ ምክንያት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን በዘመቻ መልክ ለመስጠት ሃገር አቀፍ እቅድ ተይዞ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ስለ በሽታው ስርጭትና መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች እንዲሁም በቀጣይ ቀናት ስለሚሰጡት የኮቪድ 19 ክትባት አስመልክቶ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል በተለይም የበሽታው የስርጭት መጠን ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ከህዳር 6-15/2014 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ 10 ቀናት በሃገር ደረጃ ከ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን በአስተዳደራችን ደግሞ ከ 60 ሺህ በላይ ሰዎችን ለመከተብ ዕቅድ መያዙን ወ\ሮ ለምለም ተናግረው እስካሁን ድረስም በአስተዳደራችን ሲሰጡ ከነበሩት አስትራዜኒካና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በተጨማሪ ሲኖፋርምና ፋይዘር የተባሉ ተጨማሪ የክትባት አይነቶች እንደሚሰጡና ክትባቱን በታቀደው መልኩ ለማከናወን ይቻል ዘንድም በመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ፤ በትምህርት ቤቶች ፤ በኢንደስትሪና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፤ በማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩና እንዲሁም ሌሎች ክትባቱን ማግኘት ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ክትባቱ እንደሚሰጥም ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ፡፡
ሀላፊዋ አክለውም እስካሁን ድረስ በአስተዳደራችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን 39‚544 ሰዎች መውሰድ የቻሉ ሲሆን ይህም መከተብ ካለባቸው አንፃር ሲታይ ቁጥሩ አነስተኛና ተደራሽነቱም ውስን እንደነበርና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን መውሰድም በግል ራስን ከበሽታው ከመከላከል ባሻገር ሌሎች ወገኖች ለወረርሽኙ እንዳይጋለጡ ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት በመሆኑ ማንኛውም የአስተዳደራችን ነዋሪ ራሱ ክትባቱን በመውሰድና ሌሎችም ክትባቱን እንዲወስዱ ማበረታታት እንደሚገባም ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሽታ በአሁን ወቅት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት የታየው የስርጭት መጠን ከፍተኛና አፋጣኝ መፍትሄን የሚሻ ሲሆን በነዚህ ሁለት ወራት ብቻ በአስተዳደራችን የ54 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ለፅኑ ህመምና ሞት ተጋላጭ የሚሆኑት ህሙማን በአብዛኛው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ያልወሰዱ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለውም ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና በመከተብ ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የሚያሳይ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሃገራት የክትባት ሽፋናቸውን በማሳደግ በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ውጤታማ ስራ መስራታቸውንም ሀላፊዋ አስታውቀዋል፡፡
በአሁን ወቅትም በአስተዳደራችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በበቂ መጠን ክትባቱ ለሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች በሙሉ የቀረበ በመሆኑ ነዋሪው ህብረተሰብም በክትባት ዘመቻው ወቅት ክትባቱ በሚሰጥባቸው ማዕከላት በመገኘት ክትባቱን እንዲወስድ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ፡፡


