ባለፉት በርካታ አመታት በሀገራችን በትምህርትና ስልጠና ዙሪያ በርካታ ስራዎች ሲተገበሩ የቆዩ ሲሆን በተለይም ደግሞ ከ 1987 ዓ.ም ጀምሮ የቴክኒክና ሞያ ትምህርት ስልጠና ፖሊሲና ስትራቴጂ ወቶለት ሲተገበር ቆይቷል ። ይህም በተወሰነ መልኩ ክፍተት ቢኖርበትም ነገር ግን የተሻሉ የሚባሉ ስራዎችም ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም አለማችን ከደረሰበት ወቅታዊ ሁኔታ ብሎም ሀገራችን ከደረሰችበት እድገት አንፃር ሊመጥን የሚችል አዲስ ፖሊሲና ስትራቴጂ አስፈላጊ ከመሆኑ አንፃር እንዲሁም በባለፍት የነበሩት ፖሊሲና ስትራቴጂ ክፍተቶችን ለይቶ በተሻለ መልኩ ጥራት ያለው ስልጠና ለመስጠት ዲጂታልና ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ የቲቬት አገልግሎት ለመስጠት በማለም አዲስ የቴክኒክና ሞያ ትምህርት ስልጠና ፖሊሲና ስትራቴጂ ተነድፏል ።
ይህንንም መሰረት በማድረግ አዲሱን ፖሊሲና ስትራቴጂ ምንነት ፣ አላማዎች ፣ እሳቤዎችና በተልእኮዎቹ ዙሪያ የሚመክር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በዛሬው እለት በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተዘጋጅቷል ።
በዚሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በተለይም ከፍተኛ አመራሮች ፖሊሲና ስትራቴጂውን በሚገባ ከመረዳት አንስቶ ጥልቀት ባለው መንገድ በመወያየት ተቋሙን እንዴት መደገፍ እንደሚገባ እንዲሁም ብቁ የሆነ ዜጋን በማፍራት የነዋሪውን ህብረተሰብ ጥያቄ ከመመለስ አኳያና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በምን አግባብ ማሳለጥ እንደሚገባ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አቶ ከድር ጁሀር በእለቱ ተናግረዋል ።
ቴክኒክና ሞያ ትምህርት ስልጠና ፖሊሲና ስትራቴጂ በአንድ አካል ብቻ የሚተገበር ሳይሆን የብዙ አካላትን ቅንጅት እንደሚፈልግና ከፍተኛ አመራሩ በፖሊሲና ስትራቴጂው ዙሪያ ግንዛቤ መጨበጣቸው ለቀጣይ ተፈፃሚነቱ ትልቅ እስተዋፆ እንደሚኖረው የድሬዳዋ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሮቤል ጌታቸው ተናግረው ባለፍት ጊዜያት በመደበኛነት ሲሰሩ የነበሩትን የስራ እድል ፈጠራ ወጣ ባለ መልኩ አዳዲስ የስራ አማራጮችን መሰረት በማድረግ በቀጣይ በቂ የሆነ የስራ እድል እንደሚፈጠርም አቶ ሮቤል ተናግረዋል ።


